Fana: At a Speed of Life!

በውጪ ሀገርና በሀገር ውስጥ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ድጋፍ ማድረጋቸውን አጠናክረው ቀጥለዋል

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 23፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በጀርመን ሀገር የሚኖሩ የሸዋ ሮቢትና አካባቢው ተወላጆች በጎ አድራጎት ማኅበር ግምታዊ ዋጋቸው ከ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር በላይ የሆኑ አራት የአልትራ ሳውንድ የሕክምና መገልገያ መሣሪያዎች ድጋፍ አበረከቱ።

የሕክምና ማሽኖቹ ለአራት ሆስፒታሎች የሚከፋፈሉ ሲሆን በአካባቢው ጁንታው ባደረሰው ጥፋትና ውድመት ኪሳራ የደረሰባቸውን የሕክምና ተቋማት መልሶ ለማቋቋም አጋዥ መሆናቸውንም ድጋፉን ለሆስፒታሎቹ ያስረከቡት የሸዋ ሠላምና ልማት ማኅበር ሥራ አስኪያጅ ረዳት ፕሮፌሰር ሲሳይ አውግቸው ተናግረዋል።

የአልትራ ሳውንድ የሕክምና መሣሪያዎቹ ለደብረ ብርሃን ሆስፒታል፣ ለዓለም ከተማ እናት ሆስፒታል፣ ለወረ-ኢሉ ዘውዲቱ ሆስፒታል እና ለየካቲት 12 ሆስፒታሎች ይተላለፋሉም ነው የተባለው፡፡

ድጋፉን የተረከቡት የዓለም ከተማ እናት ሆስፒታል ስራ አስኪያጅ፣ አለባቸው አቢቦ ÷ የተለገሱት ድጋፎች በጦርነቱ የተጎዱትን የሕክምና አገልግሎት መስጫ ተቋማት ዳግም መገንባት ከማስቻላቸው ባለፈ የገጠሩ ማኅበረሰብ ዘመናዊ የሕክምና አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆን በማስቻል ረገድ ትልቅ ትርጉም አላቸው ብለዋል።

የሸዋ ሠላምና ልማት ማኅበር በውጭ ሀገራት ካሉ ዳያስፖራዎች ጋር በመተባበር ጉዳት ለደረሰባቸው አካባቢዎች እና ለትምህርት ተቋማት ድጋፋቸውን አጠናክረው ለማስቀጠል እንደሚሰራም የማህበሩ ፕሬዚዳንተ ዶክተር ደረጀ ተክለማርያም ተናግረዋል።

በተጨማሪም በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገራት የሚኖሩ የደብረሲና ተወላጆች በከተማዋ በአሸባሪው ህወሓት ቤታቸው ለፈረሰባቸው ነዋሪዎች 1 ነጥብ 3 ሚሊየን ብር የሚጠጋ የቤት መሥሪያ ቁሳቁስ አስረክበዋል፡፡

የተደረገው የቆርቆሮ እና የሚስማር ድጋፍ በከተማዋ በአሸባሪ ቡድኑ ለወደሙ 50 መኖሪያ ቤቶች መሥሪያነት ይውላልም ነው የተባለው።

የፖፕሌሽንና ሚዲያ ሴንተርም በተመሳሳይ 614 ሺህ ብር ድጋፍ ለተፈናቃዮች አድርጓል።

ድጋፉንም የሲቪል ማህበራት ድርጅቶች ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጅማ ዲልቦ ከድርጅቱ ተረክበዋል።

በሌላ በኩል የኢትዮ ቴሌኮም የሰሜን ምዕራብ ሪጅን ጎንደር ሠራተኞች በምዕራብ ጎንደር ዞን ለሚገኘው የወገን ጦር 500 ሺህ ብር የሚገመት የምግብ እና የአልባሳት ድጋፍ ማድረጋቸውም ተገልጿል፡፡

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.