ምሽት ላይ በሚፈጸም ስርቆት በቂ የባቡር የትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት እንዳልተቻለ ተገለፀ
አዲስ አበባ ፣ የካቲት 17 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ምሽት ላይ በሚፈጸም የሲግናል ኮሚኒኬሽን ኬብል እና የኤሌትሪክ ገመድ ስርቆት ምክንያት በቂ የትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት እንዳልቻለ የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት አስታወቀ፡፡
አገልግሎት እየሰጡ በሚገኙ 35 ባቡሮች ላይ ምሽት ላይ በሚፈጸም የባቡር ኤሌትሪክ ገመድ እና የሲግናል ኮሚኒኬሽን ኬብል ስርቆት ምክንያት ከፍተኛ መስተጋጉል እያጋጠመ መሆኑን በአገልግሎቱ የጥገና ማዕከል ዳይሬክተርና ጊዜያዊ ስራ አስኪያጅ ተወካይ አቶ ታመነ ሽመልስ ለፋና ብሮድካስቲግ ኮርፖሬት ተናግረዋል።
ከዚህ ጋር በተያያዘም በሲ ኤም ሲ እና በሌሎች መስመሮች የትራንስፖርት ስምሪት መስተጓጎል ማጋጠሙ ተጠቁሟል።
እየተፈፀመ የሚገኘውን ስርቆት ለመከላከል ለሚመለከታቸው አካላት ማመልከታቸውን አቶ ታመነ ገልፀዋል።
የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት በግማሽ ዓመቱ አገልግሎት እየሰጡ በሚገኙት 35 ባቡሮች 72 ሚሊየን 730 ሺህ 606 ብር ገቢ ማግኘቱን ነው ያስታወቀው።
ሆኖም አሁን ላይ በመለዋወጫ እጥረት ስድስት ባቡሮች አግልግሎት እየሰጡ እንዳልሆነ የተገለፀ ሲሆን በጊዜያዊነት ብልሽት ለሚያጋጥማቸው ባቡሮች አስፈላጊው ጥገና ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በታሪክ አዱኛ