በቡራዩ ከተማ በሸኔ ሎጅስቲክስ አቅራቢነት በተጠረጠረች ግለሰብ መኖሪያ ቤት ውስጥ ከባድ መሳሪያና ጥይቶች ተያዙ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 22፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል ፊንፊኔ ዙሪያ ልዩ ዞን ቡራዩ ከተማ ነዋሪ በሆነች እና በሸኔ የሽብር ቡድን የሎጀስቲክስ አቅራቢነት በተጠረጠረች ግለሰብ መኖሪያ ቤት ውስጥ ከባድ መሳሪያና ጥይቶች ተያዙ።
የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ያካሄደውን ክትትልና ጥቆማ ለኦሮሚያ ፖሊስ በሰጠው መሰረት ተጠርጣሪዋ በቁጥጥር ስር እንድትውል መደረጓ ተገልጿል።
በተጠርጣሪዋ መኖሪያ ቤት ውስጥም በተደረገ ፍተሻ በምስራቅ ወለጋ ዞን ለሚንቀሳቀሰው የሸኔ የሽብር ቡድን ለማቀበል በዝግጅት ላይ የነበረ አንድ ብሬን ከ426 ጥይት እና 10 የብሬን ጥይት ማስቀመጫ ሰንሰለት ጋር እንዲሁም 179 የክላሽ ጥይት በቁጥጥር ስር እንዲውል መደረጉንም ከአገልግሎቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።