Fana: At a Speed of Life!

የአማራ ክልል መንግሥት  በጎንደር በተፈጠረው ግጭት በንጹሐን ሕይወት፣ አካል እና ንብረት ላይ በደረሰው ጉዳት የተሰማውን ሀዘን ገለፀ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 19፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአማራ ክልል መንግሥት  በጎንደር በተፈጠረው ግጭት በንጹሐን ሕይወት፣ አካል እና ንብረት ላይ በደረሰው ጉዳት የተሰማውን ሀዘን ገለፀ።

የክልል መንግስት በጎንደር ከተማ የተከሰተውን ግጭት አስመልክቶ መግለጫ አውጥቷል።

የመግለጫው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፦

በጎንደር ከተማ የተከሰተውን ግጭት አስመልክቶ ከአማራ ክልል መንግሥት የተሰጠ መግለጫ

የአማራ ሕዝብ በተለያዩ ቦታዎችና ዘርፈ ብዙ በኾኑ ውጫዊ እና ውስጣዊ የማጥቂያ ስልቶች የተወነጨፉበትን ቀስቶች መክቶ ሳይጨርስ በታሪካዊቷና ተቻችሎና ተከባብሮ የመኖር ተምሳሌት በኾነችው ጎንደር ከተማ ውስጥ ሃይማኖትን ሽፋን ያደረገ ግጭት በመቀስቀስ የሕዝቡን አንድነት ለመስበር ጥረት ተደርጓል።

በዛሬው ዕለት የጎንደር ከተማ ነዋሪ እና የጎንደር ሕዝበ ሙስሊምና ሕዝበ ክርስቲያኑ እንዲሁም የኹሉም አባት የነበሩት ታላቁ ሸኽ ከማል ለጋስ ሥርዐተ ቀብር እየተፈጸመ በነበረበት ሰዓት ከቀብር ቦታው ጋር ድንበርተኛ የኾነው ቤተ ክርስቲያን ላይ ለቀብር የሚሆን ድንጋይ “እናነሳለን የመስጊዱ ክልል ነው፤ አታነሱም የቤተ ክርስቲያኑ ቅጥር ነው” በሚል በተወሰኑ ግለሰቦች መካከል በተጀመረ ግጭት የሰው ህይወት ጠፍቷል፤ የአካል ጉዳትም ደርሷል። የተለያዩ ንብረቶችና ተቋማትን የማጥፋት እንቅስቃሴዎችም ተስተውለዋል።

በተፈጠረው ግጭት በንጹሐን ሕይወት፣ አካል እና ንብረት ላይ በደረሰው ጉዳት የክልሉ መንግሥት ጥልቅ ሐዘን የተሰማው መሆኑን እየገለጽን ለተጎጂ ቤተሰቦችም መጽናናትን እንመኛለን፡፡

የአማራ ክልል መንግሥት በማንኛውንም አይነት የጽንፈኝነት አስተሳሰብ የሚፈጠር የሰላም መደፍረስንም ኾነ በንጹሐን ሕይወት፣ አካልና ሀብት ንብረት ላይ የሚደርስን ጥፋትን የሚሸከምበት ጫንቃ የለውም፡፡ ስለኾነም በጥፋተኞች ላይ አስፈላጊውን ኹሉ ሕጋዊ እና ተመጣጣኝ እርምጃም ይወስዳል፡፡

በአሁኑ ሰዓት የክልሉ መንግሥት የተከሰተውን ግጭት ለማብረድ፤ በድርጊቱ የተሳተፉትንና ግጭቱን እያባባሱ ያሉ አካላትንም በቁጥጥር ሥር ለማዋል የክልላችን የጸጥታ ኃይል፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ሰላም ወዳድ የኾኑት የጎንደር ከተማ ወጣቶች ጋር ተቀናጅቶ ውጤታማ ሥራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል።

በመኾኑም አካባቢውን በማረጋጋት እና ሕግና ሥርዐትን በማስከበር ግጭቱን በቁጥጥር ሥር ለማዋል ተችሏል፡፡

የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በሰው ሕይወትና ንብረት ላይ የደረሰውን የጉዳት መጠንና ሌሎች አስፈላጊ መረጃዎችን በማሳባሰብ ለሕዝቡ ትክክለኛ መረጃዎችን የመግለጽ፣ የወንጀሉ ተጠርጣሪዎችን በሕግ ጥላ ሥር የማዋል፣ ተጎጅዎች ድጋፍ እንዲደረግላቸው የማጣራት ሥራዎችን በማከናወን ለሕዝብ የሚያሳውቅ ይኾናል፡፡

መላው የጎንደር ከተማ ሕዝብ ራሱን፣ አካባቢውና እና ከተማውን በማረጋጋትና በመጠበቅ የበኩሉን አስተዋጽኦ በመወጣት መንግሥት አጥፊዎችን በሕግ ፊት ለማቅረብ እያከናወነ የሚገኘውን እንቅስቃሴ ከጸጥታ ኃይላችን ጎን በመኾን በተለመደው ሁኔታ ትብብሩን እንዲያስቀጥል እንጠይቃለን፡፡

ሚያዚያ 18 ቀን 2014 ዓ.ም.

የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት

ባሕር ዳር

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.