Fana: At a Speed of Life!

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ለፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ የደስታ መልዕክት አስተላለፉ

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 14 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የቻይናው ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ በድጋሚ የቻይናው ኮሚዩኒስት ፓርቲ ዋና ፀሀፊ ሆነው በመመረጣቸው የእንኳን ደስ ያልዎት መልዕክት አስተላለፉ።
 
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው የእርሳቸው በድጋሚ መመረጥ፥ የቻይናን ህዝብ በቀጥታ ተጠቃሚ ያደረጉ ዘርፈ ብዙ ስኬቶች የእርሳቸውን ውጤታማ የአመራር ብቃት ያረጋገጠ መሆኑን ጠቅሰዋል።
 
በአመራር ዘመናቸው የቻይናን ኢኮኖሚያዊ እድገትን ከማስቀጠል ባለፈ የሀገሪቱን ዓለም አቀፍ ተፅዕኖ ፈጣሪነትን በማሳደግ በኩል ትልቅ ሚና መጫወታቸውንም አንስተዋል።
 
አሁን ላይም ዓለም የቻይናን ኮሚዩኒስት ፓርቲ ሀገር በቀል የልማት ሞዴልን ጠቃሚነት እንደሚረዳ እምነቴ ነው ብለዋል በመልዕክታቸው።
 
ኢኮኖሚያዊ እድገትን በማረጋገጥ እና በዜጎች መካከል ያለውን የኑሮ ልዩነት ለማጥበብ ያደረጉት ያልተቋረጠ ጥረትም እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ታዳጊ ሀገራት ጥሩ ተሞክሮና ትምህርት ነው ሲሉም ገልጸዋል።
 
ኢትዮጵያ ከፓርቲው በርካታ ልምዶችን ቀስማለች ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ በተለይም በሰው ተኮር ልማት፣ በውጤታማ አስተዳደር እንዲሁም በሕዝብ አገልግሎት አሰጣጥ ረገድ መልካም ተሞክሮ መውሰዷን አንስተዋል፡፡
 
በእርስዎ አስተዳደር ቻይና የኢትዮጵያ ስትራቴጂካዊ አጋር ሀገር ናት ሲሉም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገለጹት፡፡
 
በቀጣይም በተለያዩ ዘርፎች የሀገራቱን ሕዝቦች ጥቅም ባስከበረ መልኩ በትብብር እንደሚሰራ አንስተዋል፡፡
 
የሺ ጂንፒንግ ዳግም መመረጥም የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ ከብልጽግና ፓርቲ ጋር ያለውን ግንኙነት እና ትብብር ይበልጥ ያጠነክረዋል ነው ያሉት፡፡
 
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የብልጽግና ፓርቲ በቀጣይ ከቻይናው ኮሚኒስት ፓርቲ ጋር በትብብር ለመስራት ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡
 
 
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.