Fana: At a Speed of Life!

የሰላም ስምምነቱ  በሀገሪቱ ሰላምን ለማስፈንና ልማትን ለማረጋገጥ መሰረት የሚጥል ነው-የሐረሪ ክልል

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 27፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሰላም ስምምነቱ በሀገሪቱ ሰላምን ለማስፈንና ልማትን ለማረጋገጥ መሰረት የሚጥል እና መንግስትና ህዝባችን ፊቱን ሙሉ በሙሉ ወደ ልማት እንዲያዞሩ እድል የሚፈጥር ነው ሲል የሐረሪ ክልል ገለፀ፡፡

በኢትዮጵያ መንግስትና በሕወሀት መካከል የተደረሰውን  የሰላም ስምምነት አስመልክቶ የሐረሪ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት መግለጫ  አውጥቷል፡፡

በመግለጫው÷ በአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ በኢትዮጵያ መንግሥት እና በህወሓት መካከል የተፈረመው የሰላም ስምምነት   የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት፣ የግዛት አንድነት እና ዘላቂ ሰላም በሚያረጋግጥ የተጠናቀቀ መሆኑ ተመላክቷል።

የሰሜኑ ጦርነት በሰላም ለመቋጨት የተፈረመው የሰላም ስምምነት በሀገሪቱ ሰላምን ለማስፈንና ልማትን ለማረጋገጥ መሰረት የሚጥል እና መንግስትና ህዝባችን ፊቱን ሙሉ በሙሉ ወደ ልማት እንዲያዞሩ እድል የሚፈጥር ከመሆኑም ባሻገር በጦርነቱ ምክንያት የተጎዱ ወገኖችን ለመደገፍና የወደሙ መሰረተ ልማቶችን መልሶ ለመገንባት ያስችላል።

መንግስት ከጅምሩም ቢሆን ለሰላም ያለውን ቁርጠኝነት በተደጋጋሚ ማሳየቱ የሚታወስ ሲሆን የሰላም ውይይቱም በአፍሪካ ህብረት እንዲካሄድ የኢትዮጵያ መንግስት የያዘው አቋም ውጤት አምጥቷል ብሏል ክልሉ።

በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት በኢትዮጵያ መንግስትና በህወሃት መካከል የተፈረመው የሰላም ስምምነት የአፍሪካውያን ችግሮቻቸውን በራሳቸው መፍታት እንደሚችሉ በተግባር የታየበት ፤ከዚህ ባሻገር የሀገራችንን ሰላም እና የጀመርነውን የብልፅግና ጉዞ እውን እንዲሆን የማይፈልጉ አካላትን አንገት ያስደፋ ሆኗል ሲልም በመግለጫው አስፍሯል።

የሐረሪ ክልል መንግስትና ህዝብ በተደረሰው የሰላም ስምምነት በአግባቡ ተፈፃሚ እንዲሆን በሙሉ ልብ ከመደገፍ ባሻገር በጦርነት ጉዳት የደረሰባቸውን አካባቢዎች መልሶ ለመጠገን በሚደረገው ጥረት የሚጠበቅበትን አስተዋጽኦ ሁሉ ለማበርከት ዝግጁ መሆኑንም ገልጿል።

የጉዳቱ ሰለባ የሆኑ ወገኖችን መልሶ ለማቋቋም፣ የወደሙ ተቋማትን መልሶ ለመገንባት ለሚደረጉ ጥረቶች በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚገኝ ሁሉም አገር ወዳድ ዜጋ በአንድነት በመሰለፍ ድጋፉን ማሳየት  እንደሚገባውም መልእክቱን አስተላልፏል ክልሉ።

በኢትዮጵያ መንግስት እና በሕወሃት መካከል ስምምነት የተደረሰባቸው ጉዳዮች ተግባራዊ እንዲሆኑ እና በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ሁሉም ዜጋ የበኩሉን አስተዋጽኦ በማበርከት አገራዊ ግዴታውን እንዲወጣም ክልሉ ጥሪውን አቅርቧል።

የሰላም ስምምነቱ  በዚህ መልኩ እንዲጠናቀቅ ለደከሙና የህይወት ዋጋ ለከፈሉ ሁሉ ታላቅ ክብር ይገባቸዋል ሲልም የሐረሪ ክልል ባወጣው መግለጫ አስፍሯል።

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.