Fana: At a Speed of Life!

ከሕገ ወጥ ግንባታ ጋር ተያይዞ 12ሺህ ብር ጉቦ የተቀበሉ የደንብ አስከባሪዎች ተቀጡ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 15፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ሕገ ወጥ ግንባታ ማስቆም ሲገባቸው 12 ሺህ ብር ጉቦ የተቀበሉ አምስት የደንብ አስከባሪዎች በእስራትና በገንዘብ ተቀጡ።

የቅጣት ውሳኔውን ያስተላለፈው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 2ኛ የጸረ ሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ነው፡፡

ተከሳሾቹ ብሩክ አበበ አድማሱ ፣ሀብታሙ ጂልቻ ደበሌ፣ ሀይሉ ከበደ መቆያ፣ ትእግስት ሰብስቤ ላቀው እና ጫላ ከበደ ጉርሜሳ የተባሉ ግለሰቦች ናቸው፡፡

የዐቃቤ ሕግ ክስ እንደሚያስረዳው ተከሳሾቹ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 12 የደንብ ማስከበር ጽህፈት ቤት ውስጥ የደንብ ማስከበር ኦፊሰር በመሆን እያገለገሉ በነበሩበት ወቅት፤ በየካቲት 6 ቀን 2013 ዓ.ም በግምት ከቀኑ 6:00 ሰአት ሲሆን ፥ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 12 ልዩ ቦታው ጨሬ ሰፈራ ተብሎ ከሚጠራው ስፍራ ወንጀሉን መፈጸማቸውን ነው፡፡

በዚሁ ስፍራ የግል ተበዳይ ጉኡሽ ተስፋየ የተባለው ግለሰብ በመኖሪያ ጊቢ ውስጥ ያለ ግንባታ ፈቃድ ግንባታ ሲያከናውን በስራ ኃላፊነታቸው ስራውን ማስቆም ሲገባቸው ኃላፊነታቸውን ወደ ጎን በመተው ጉቦ መጠየቃቸውን የዐቃቤ ሕግ ክስ አስረድቷል፡፡

1ኛ፣2ኛ፣3ኛ እና 4ኛ ተከሳሾች በጋራ በመሆን 1ኛ ተከሳሽ ተበዳይን 10 ሺህ ብር ስጠንና ስራውን ትቀጥላለህ ማለታቸውም በክሱ ሰፍሯል፡፡

ተከሳሾቹ በቀን በየካቲት 6 ቀን 2013 ዓ.ም ከቀኑ ስድስት ሰዓት በድጋሚ ወደ ተበዳይ ቤት ሄደው 1ኛ ተከሳሽ 10 ሺህ ብር ያንሳል ጨምር በማለት መደራደሩን እና 12 ሺ ብር ከተበዳይ 1ኛ እና 2ኛ ተከሳሾች ተቀብለው ከ3ኛ እና 4ኛ ተከሳሾች ጋር የተከፋፈሉ መሆኑ በክሱ ተገልጿል፡፡

5ኛ ተከሳሽ ደግሞ የከሰአት ፈረቃ ላይ የሚሰራ የደንብ ማስከበር ኦፊሰር ሲሆን ፥ በተከሳሾች የተበዳይን ግንባታ እንዳይቃወም ተነግሮት 1 ሺህ ብር የተሰጠውና የተቀበለ በመሆኑ ተከሳሾች በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን በፈጸሙት ጉቦ መቀበል ወንጀል ነው የተከሰሱት፡፡

ዐቃቤ ሕግም ወንጀሉን መፈጸማቸውን የሚያስረዱ ሁለት የሰው ምስክሮችን ጨምሮ የሰነድ ማስረጃዎችን ለፍርድ ቤቱ አቅርቧል፡፡

የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 2ኛ የፀረሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ተከሳሾቹ የቤተሰብ አስተዳዳሪ መሆናቸውን፣ ከዚህ ቀደም የወንጀል ሪከርድ የሌለባቸው መሆኑን በቅጣት ማቅለያ ወስዷል፡፡

በዚህም ተከሳሾቹን ከ4 ወር እስከ 6 ወር በሚደርስ ቀላል እስራትና እያንዳንዳቸው በ500 ብር እንዲቀጡ ወስኗል፡፡

በዙፋን ካሳሁን

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.