Fana: At a Speed of Life!

በሶማሌ ክልል ድርቅ የመቋቋም አቅም የሚገነቡና የእንስሳት እርባታን የሚያዘምኑ ፕሮጀክቶች ይፋ ሆኑ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 15፣ 2015(ኤፍ ቢ ሲ) በሶማሌ ክልል የአርብቶ አደሩን ድርቅ የመቋቋም አቅም የሚገነቡ እና የእንስሳት እርባታ ልማትንና ግብይትን የሚያዘምኑ የ161 ሚሊየን ዶላር ፕሮጀክቶች ይፋ ሆኑ።

ፕሮጀክቶቹ በዓለም ባንክና በአፍሪካ ልማት ባንክ የገንዘብ ድጋፍ የሚተገበሩ ናቸው ተብሏል።

ለፕሮጀክቶቹ ከዓለም ባንክ 115 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ከአፍሪካ ልማት ባንክ ደግሞ 46 ሚሊየን ዶላር በድምሩ 161 ሚሊየን ዶላር መመደቡን የቢሮው ኃላፊ አቶ መሐመድ ሼህ አደን ገልጸዋል።

እንደ ኃላፊው ገለጻ ፕሮጀክቶቹ የአርብቶ አደሩን ማሕበረሰብ የፋይናንስ አገልግሎት ተጠቃሚነትን ለማጠናከር፣ ከአየር ንብረት ለውጥ አደጋዎች ለመከላከል፣ የእንስሳት እርባታ ልማትና ግብይትን ለማዘመን የሚያስችሉ ናቸው።

ፕሮጀክቶቹ በክልሉ ሁሉም ዞኖች የሚገኙ አርብቶ አደሮችን ተጠቃሚ እንደሚያደርጉም ገልጸዋል።

ለአምስት ዓመታት በሚቆዩት ፕሮጀክቶች 4 ነጥብ 5 ሚሊየን አርብቶ አደሮች እንዲሁም በእንሳሳት ንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩ ማህበራትና ነጋዴዎች ተጠቃሚ ይሆናሉ ተብሏል።

የሶማሌ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ መሐመድ ዩሱፍ ፥ የፕሮጀክቶቹ መጀመር አርብቶ አደሩን ከፋይናንስ ተቋማት ጋር በማስተሳሰር ለእንስሳት ሀብቱ የአደጋ ዋስትና እንዲያገኝ ከማድረግ ባለፈ በቀላሉ ወደ ገበያ የሚደርስበትን ሰንሰለት ምቹ ያደርጋል ብለዋል።

በፕሮጀክቶቹ አተገባበር ላይ ገለጻ ለማድረግ በጅግጅጋ ከተማ በተዘጋጀ መርሀ-ግብር የክልል እና የወረዳ የሥራ ኃላፊዎች መገኘታቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.