Fana: At a Speed of Life!

በባንኮች የሚሰጠው ብድር ፍትሃዊ እና የብዙሃኑን ተጠቃሚነት ያረጋገጠ ሊሆን ይገባል- አቶ ማሞ ምህረቱ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 20፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በባንኮች የሚሰጠው ብድር ፍትሃዊ እና የብዙሃኑን ተጠቃሚነት ያረጋገጠ እንዲሆን በቅንጅት መስራት እንደሚገባ የብሄራዊ ባንክ ገዥ አቶ ማሞ ምህረቱ ገለጹ፡፡

አቶ ማሞ ÷ አሁን ላይ በመላው ኢትዮጵያ 11 ሺህ የሚሆኑ ቅርጫፎች ያሏቸው 31 ባንኮች ለደንበኞቻቸው አገልግሎት እየሠጡ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡

የባንክ ቅርንጫፎች መብዛት ከዘመናዊ ቴክኖሎጂ ጋር ተዳምሮ የፋይናንስ ተደራሽነትን ከማስፋት ባሻገር ለቁጠባና ኢንቨስትመንት የሚውል የፋይናንስ ሃብት በማሰራጨት ለኢኮኖሚ ግንባት ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው ብለዋል፡፡

ባንኮች እስከ መጋቢት 2015 መጨረሻ ድረስ ከ123 ነጥብ 6 ሚሊየን በላይ ተቀማጭ የሒሳብ አካውንት የከፈቱ ሲሆን÷ ከ2 ነጥብ 06 ትሪሊየን ብር በላይ ተቀማጭ ገንዝብ መሰብሰባቸውንም አንስተዋል፡፡

ባንኮች የሚሰበስቡት የብድር መጠን አንዳንድ ችግሮች ቢኖሩትም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱን ነው አቶ ማሞ የገለጹት፡፡

ባንኮች ቀስ በቀስ እራሳቸውን ከዘመኑ ቴክኖሎጂ ጋር በማቆራኘት እና ለዜጎች በዲጂታል የታገዘ የባንክ አገልግሎት በመስጠት ኢትዮጵያ የጀመረችውን የተደራሽነትን እቅድ እያሳኩ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

እየዘመነ ከመጣው የባንክ አገልግሎት አሰጣጥ ጋር ተወዳዳሪ እና ተመራጭ ለመሆንም ባንኮች በሰው ሃይል፣ በቴክኖሎጂና በአሰራር ስርዓት እራሳቸውን ማዘመን አለባቸው ብለዋል፡፡

በተለይም አሁንላይ የሚስተዋልባቸውን የአቅም ውስንነት ግምት ውስጥ በማስገባት ጠንካራ የካፒታል አቅም መፍጠር ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት፡፡

የፋይናንስ ዘርፉን ሌሎች የውጭ ባለድርሻ አካላት እንዲቀላቀሉት የማድረግ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመው÷ የሀገር ውስጥ ባንኮችም የቤት ስራቸውን አስቀድመው እንዲያከናውኑ አሳስበዋል፡፡

ብሔራዊ ባንክ የፋይናንስን ጤናማነት፣ አስተማማኝነት እና አካታችነት ይበልጥ ማረጋገጥ የሚያስችል በአይነቱ እና በይዘቱ ዘርፈ ብዙ ሊባል የሚችል ማሻሻያ ስራ ለመተግበር እንቅስቃሴ መጀመሩንም አንስተዋል፡፡

በባንኮች የሚሰጠው የብድር ሁኔታ ፍትሃዊ እና የብዙሃኑን ተጠቃሚነት ያረጋገጠ እንዲሆን በተለይም አምራች ዘርፉን እንዲደግፍ በቅንጅት መስራት እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.