Fana: At a Speed of Life!

የብራዚል ባለሀብቶች በኢንዱስትሪ ፓርኮች ኢንቨስት እንዲያደርጉ የሚያስችል ስምምነት ተደረሰ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 11፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የብራዚል ባለሀብቶች በኢንዱስትሪ ፓርኮች ኢንቨስት እንዲያደርጉና በፓርኮች የሚገኙ አምራቾች በብራዚል ተጨማሪ የገበያ መዳረሻዎችን እንዲያገኙ የሚያስችል ስምምነት ተደርሷል።

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ አክሊሉ ታደሰ በኢትዮጵያ የብራዚል አምባሳደር ጃንዲር ፌሬራ ዶሳንቶስ ጋር ተወያይተዋል።

በውይይታቸውም ኢትዮጵያና ብራዚል በዘርፈ ብዙ መስኮች ለረጅም ዓመታት የዘለቀ ግንኙነታቸውን በኢንቨስትመንትና ተያያዥ ጉዳዮችም ማጠናከር በሚቻልባቸው ዝርዝር ጉዳዮች ላይ ሀሳብ ተለዋውጠዋል።

የብራዚል ባለሀብቶች በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ እንዲያመርቱ እንዲሁም አምራች ኩባንያዎች ምርቶቻቸውን በብራዚል ገበያ መሸጥ እንዲችሉ የገበያ ትስስር እንዲፈጥሩ ለማስቻል ከስምምነት ደርሰዋል።

በማኑፋክቸሪንግ በተለይም በአግሮፕሮሰሲንግ ዘርፍ ብራዚል ተሞክሮዋን በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ስር ወዳሉ ኢንቨስትመንቶች ማስፋፋት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ምክክር ተደርጓል፡፡

ኢትዮጵያ በአግሮፕሮሰሲግ ዘርፍ እምቅ አቅም እንዳላት የገለጹት በኢትዮጵያ የብራዚል አምባሳደር  ጃንዲር ፌሬራ ዶሳንቶስ÷ በዘርፉ የተሰማሩ ባለሀብቶች በብራዚል ያለውን ተሞክሮ እንዲያገኙ ለማስቻል እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።

በቀጣይም የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ የቢዝነስ ፎረም በጋራ ይዘጋጃል መባሉን ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.