Fana: At a Speed of Life!

የመንግስት ዲጂታል የግዥ ካርድ ይፋ ሆነ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 25፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የገንዘብ ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የጋራ ፕሮጀክት የሆነው የመንግስት ዲጂታል የግዥ ካርድ ይፋ ሆነ።

የገንዘብ ሚኒስትር ዴዔታ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) እና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖን ጨምሮ የመንግስት ተቋማት የፋይናንስ የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት በፌዴራል የመንግስት ተቋማት የኤሌክትሮኒክስ ክፍያ አተገባበር ዙሪያ ውይይት ተካሂዷል።

በዕለቱ ይፋ የሆነው የመንግስት ዲጂታል የግዥ ካርድ ተቋማት የዲጂታል ግዥ ለመፈጸም የሚያስችል ሲሆን÷ የመንግስት ወጪ በአግባቡ ለመጠቀም የሚያስችል ነው ተብሏል።

በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ170 በላይ የሚሆኑ ተቋማት በኤሌክትሮኒክስ የግብይት ስርዓት የገቡ ሲሆን÷ ባለፈው በጀት ዓመት 3 ነጥብ 3 ትሪሊየን የገንዘብ ግብይት መፈፀሙ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቤ ሳኖ÷ የኤሌክትሮኒክስ የግብይት ስርዓት በአጭር ጊዜ ለውጥ እያመጣ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በዕለቱ ይፋ ከሆነው የመንግስት የግዥ ካርድ በተጨማሪ ሌሎች የክፍያ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችሉ አሰራሮች እንደሚጀመሩ ተናግረዋል።

የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ የግዥ ካርድ ፕሮጀክቱን ውጤታማ ለማድረግ በትብብር እንደሚሰራ ገልጸዋል።

የመንግስት ግብይት በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ስርዓት ትልቅ ድርሻ ስላለው ከባንኩ ጋር የሚሰሩ ስራዎች ትልቅ ለውጥ ያመጣሉ ብለዋል፡፡

በየጊዜው የሚነሱ ቅሬታዎችን ለመፍታት የተሻለ አገልግሎት ማቅረብ ይገባል ያሉ ሲሆን የሚመለከታቸው አካላት በፍጥነት ወደዚህ ዘመናዊ አሰራር እንዲገቡ አሳስበዋል።

የዲጂታል ክፍያ ስርዓትን ዕውን ማድረግ የክፍያ ስርዓትን ከማሻሻል ባለፈ የፋይናንስ ተጋላጭነት በመቀነስ በኩል ፋይዳው የጎላ ነው መባሉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በሂደትም አጠቃላይ የዲጂታል ስርዓትን በማስፋፋት ይህ አገልግሎት ከሌሎች ባንኮች ጋርም ክፍያ መፈፀም የሚያስችል እንዲሆን ይሰራል ተብሏል፡፡

በበጀት ዓመቱ በዲጂታል አገልግሎት የተሻለ አፈፃፀም የነበራቸው ተቋማት ዕውቅና ተሰጥቷቸዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.