Fana: At a Speed of Life!

ከቤት ጠፍታ በ3 ማይሎች ርቀት በሚገኝ ጫካ ውስጥ የተገኘች የ2 አመት ህጻን

አዲስ አበባ፣ መስከረም 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአሜሪካ ሚቺጋን የጠፋችው የ ሁለት ዓመት ህጻን ሶስት ማይሎችን በባዶ እግሯ ተጉዛ ጫካ ውስጥ መገኘቷ ተሰምቷል፡፡

በአሜሪካ ሰሜን ሚቺጋን በምትገኝ ፌዞርን ከተማ የሚገኙት ቤተሰቦቿ ህጻን ቴአ ቼዝ ከቤት መጥፋቷን ለግዛቱ ፖሊስ ካሳወቁ ከአራት ስዓታት በኋላ በሶስት ማይሎች ርቀት የሚገኝ ጫካ ውስጥ ውሻ ተንተርሳ ተኝታ መገኘቷን የሲኤንኤን ዘገባ አመላክቷል፡፡

የቴአ እናት ብሩክ ቼዝ ሁኔታውን ስታስረዳ÷ በግቢ ውስጥ የምትጫወት ሴት ልጇን ጫማ ስላላደረገች ወደቤት እንዲያስገባት ለአጎቷ መናገሯንና አጎቷም ወደመጫዎቻ ቦታዋ ሲሄድ እንዳላገኛት ከዛም በኋላ በድንጋጤ ለፖሊስ ማመልከታቸውን ትገልጻለች፡፡

በቤታቸው ግቢ ውስጥና አቅራቢያ ለ20 ደቂቃ ከህጻኗ አጎት ጋር ፍለጋ ካደረጉ በኋላም በሁኔታው በመደናገጥ ለህጻኗ አባትና ለፖሊስ መደወላቸውን ተናግራለች፡፡

“ልጄ ቴአ መጥፋቷን የሚያረዳ የስልክ ጥሪ በደረሰኝ ጊዜ ምንም ነገር ማሰብ አልቻልኩም በሁኔታው በጣም ተደናግጬ ነበር” ይላል የህጻኗ አባት ጃኑንዚዮ ክስተቱን ሲያስታውስ፡፡

ህጻን ቴአ መጥፏቷ ከተረጋገጠ በኋላ የሚቺጋን ፖሊስ በድሮን ታግዞ ፍለጋውን ቀጠለ።

የአካባቢው ነዋሪዎች ደግሞ የራሳቸውን የፍለጋ ቡድን በመመስረት ህጿኗ ትገኝበታለች ብለው የጠረጠሩትን ቦታ ሁሉ ማሰሳቸውን የህጻኗ አባት ተናግሯል ፡፡

የአካባቢው ፖሊስ ህጻኗን ፍለጋ በጀመረ በአራት ሰዓታት ውስጥ የሁለት ዓመቷ ህጻን በባዶ እግሯ ከቤተሰቧ ውሾች ጋር ሶስት ማይል ተጉዛ ጫካ ውስጥ አንዱን ውሻ ተንተርሳ እንቅልፏን ተኝታ ማግኘቱን ገልጿል፡፡

ህጻኗ ተኝታ የተገኘችበት ጫካ የሙቀት መጠን ወደ 60 ዲግሪ ሴንቲግሬድ እንደነበር የተገለጸ ቢሆንም ህጻኗ በተደረገላት የህክምና ክትትል በመልካም ጤንነት ላይ እንደምትገኝ ዘገባው አስታውሷል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.