Fana: At a Speed of Life!

አዲስ አበባ ስታዲየም የሳር ንጣፍ ሥራ በቅርቡ ለማስጀመር እየተሰራ ነው ተባለ

 

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 25፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) መመዘኛ መስፈርትን ተከትሎ እድሳት እየተደረገለት ያለው የአዲስ አበባ ስታዲየም የሳር ንጣፍ ሥራ ለማስጀመር እየተሰራ መሆኑን የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ገለጸ።

ለበርካታ ዓመታት በኢትዮጵያ ዓለም አቀፋዊና አህጉራዊ ጨዋታዎችን በብቸኝነት ሲያስተናግድ የነበረው የአዲስ አበባ ስታዲየም በካፍና ፊፋ የተቀመጠውን መመዘኛ ባለማሟላቱ ጨዋታዎችን እንዳያስተናግድ መታገዱ ይታወቃል።

ይህን ተከትሎም ስታዲየሙን ወደ ሥራ ለማስገባት ሰኔ 2013 ዓ.ም ጨረታ ወጥቶ የመጀመሪያው ምዕራፍ እድሳት ሥራ መጀመሩ የሚታወስ ሲሆን÷ ለእድሳቱ በመንግሥት በኩል 150 ሚሊየን ብር መመደቡን ከባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የጽሕፈት ቤት ኃላፊ ባህሩ ጥላሁን÷ የአዲስ አበባ ስታዲየም የሲቪል ምህንድስና ሥራ ቢጠናቀቅም የሳር ንጣፍ ሥራው እስከ አሁን አለመጀመሩን መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በኢትዮጵያ በሲቪል ምህንድስናው ብቃታቸው የተረጋገጠ ተቋማትና ባለሙያዎች ቢኖሩም ከሳር ንጣፍ ጋር በተያያዘ በዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማኅበር (ፊፋ) ፈቃድ ያገኘ ድርጅት እንደሌለ አመልክተው ይህም የስታዲየሙን የእድሳት ሥራ እንዲጓተት ማድረጉንና ለጉዳዩ አፋጣኝ መፍትሔ መስጠት እንደሚገባው ጠቁመዋል።

የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት በበኩላቸው÷ ከሳር ንጣፍ ሥራውን ከፈረንሳይና ከቱርክ እንዲሁም ከሌሎች አገራት ባለሙያዎችን አምጥቶ ሥራውን ለማከናወን የዋጋ ጉዳይ ላይ ውይይት እየተደረገ እንደሚገኝና በቅርቡ ሥምምነት ላይ ይደረሳል ተብሎ እንደሚጠበቅም ጠቁመዋል።

በሁለተኛው ምዕራፍ የስታዲየሙን እድሳት ሥራ በፍጥነት ለመጨረስ አስፈላጊው ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝም አመልክተዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.