Fana: At a Speed of Life!

የባሕር በር ስምምነቱ የሚደገፍ ሀገራዊ አጀንዳ ነው – የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ም/ቤት

አዲስ አበባ፣ ጥር 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ከሶማሊ ላንድ ጋር ያደረገችው የባሕር በር ስምምነት በቅንነት የሚወሰድ ሀገራዊ አጀንዳ በመሆኑ ለተግባራዊነቱ ድጋፍ እንደሚያደርጉ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባላት አስታወቁ፡፡

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከአባላቱ ጋር ምክክር አድርጓል።

በኢትዮጵያና ሶማሊ ላንድ መካከል በተደረሰው የመግባቢያ ስምምነት ዙሪያም የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የጋራ ምክር ቤቱ አባላትም ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት እንዳሉት÷ በመግባቢያ ስምምነቱ ዙሪያ የተሰጠው ማብራሪያ የሚሰሙ ብዥታዎችን የሚያጠራ ብሎም በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመቆም የሚያስችል ነው፡፡

የጋራ ምክር ቤቱ ሰብሳቢ ደስታ ዲንቃ÷ የጋራ ምክር ቤቱ የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ልማትና እድገት የሚሻ በመሆኑ በመንግሥት የተጀመረው ጥረት እንዲሳካ ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል፡፡

የጋራ ምክር ቤቱ ምክትል ሰብሳቢ መለሰ ዓለሙ በበኩላቸው÷ የፖለቲካ ፓርቲዎች የግል ፖለቲካዊ አቋም ቢኖራቸውም በወሳኝ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ግን ልዩነት የላቸውም ብለዋል፡፡

የኢዜማ ምክትል መሪ ዮሐንስ መኮንን (አርክቴክት)÷ ፓርቲያቸው በተለያዩ ሀገራዊ የፖሊሲ ጉዳዮች ከመንግሥትና ሌሎች ፓርቲዎች ጋር ልዩነት ቢኖረውም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም እና አጀንዳዎች ላይ ግን የተለየ አቋም እንደሌለው አመላክተዋል፡፡
የአፋር ሕዝብ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ፓርቲ ሊቀ-መንበር መሃሙዳ ጋዓስ÷ ኢትዮጵያ የነበራትን የባሕር በር በማጣቷ ብዙ ችግር ማስተናገዷን ጠቅሰው፤ አሁን ላይ ባለቤት የሚያደርጋት ጥረት መጀመሩ የሚደነቅ ነው ብለዋል።

ከኢትዮጵያ አሁናዊ ኢኮኖሚ ዕድገት አኳያ አማራጭ ወደቦችን ማስፋት ተገቢ በመሆኑ ከሶማሊ ላንድ ጋር የተደረሰው ስምምነት ተግባራዊ እንዲሆን የጋራ ፍላጎታችን ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
የአንዲት ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀ-መንበር ሲሳይ ደጉ÷ ከሶማሊላንድ ጋር የተደረሰው ስምምነት ይበል የሚያሰኝ እና ለቀጣናው ትብብርም መልካም ጅማሮ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም የባሕር በር ስምምነቱን ተግባራዊነት እንደሚደግፉ ገልጸው፤ መንግሥት ውስጣዊ አንድነትን የሚሸረሽሩ የሰላምና ጸጥታ ሥራዎችን መፍታት እንዳለበት አመላክተዋል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- FBC (Fana Broadcasting Corporate S.C.)
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.