Fana: At a Speed of Life!

የአማራ ክልል የሠላም ሁኔታ መሻሻል የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎችን ለመመለስ ዕድል መፍጠሩ ተጠቆመ

አዲስ አበባ፣ ጥር 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በክልሉ እየተሻሻለ የመጣው የሠላም ሁኔታ የልማትና የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎችን ለመመለስ ዕድል መፍጠሩን በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊ ይርጋ ሲሳይ ገለጹ።

የአማራ ክልልና የደሴ ከተማ አሥተዳደር ከፍተኛ አመራሮች በደሴ ከተማ በግንባታ ላይ የሚገኙ የመሠረተ ልማት ሥራዎችን ጎብኝተዋል።

አቶ ይርጋ በጉብኝታቸው ወቅት እንዳሉት÷ አሁን ላይ በክልሉ ያለውን ሠላም ዘላቂ ለማድረግ በሁሉም አካባቢ ሕብረተሰቡን የማሳተፍ ሥራ እየተሠራ ነው፡፡

በደሴ ከተማ የሚታዩ የመሠረተ ልማት ግንባታዎችን ለማፋጠን የተፈጠረውን ምቹ ሁኔታ በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባም ገልጸዋል።

የተጀመሩ፣ ተጀምረው የተቋረጡና በአዲስ መልክ የሚጀመሩ የልማት ፕሮጀክቶችን አጠናክሮ በማስቀጠል የሕዝብ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ሕዝቡ ለሠላም መጠበቅ ቅድሚያ ሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

የደሴ ከተማ አስተዳደር የከተማና መሠረት ልማት መምሪያ ሥራ አስኪያጅ ቃሲም አበራ በበኩላቸው ÷ በከተማዋ ከ1 ቢሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተለያዩ የመሠረተ ልማቶች እየተገነቡ ነው ብለዋል።

ከመሠረተ ልማት ግንባታዎቹ መካከል ዛሬ የተጎበኙት የደሴ ዘመናዊ መናኸሪያ ፣ 7 ነጥብ 8 ኪሎ ሜትር የአስፋልት መንገድ፣ ድልድይና ሌሎች የመሰረተ ልማት ግንባታዎች ይገኙበታል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በመንግሥት በጀትና በሕዝቡ የገንዘብ ድጋፍ የሚገነቡት ፕሮጀክቶቹ በተያዘላቸው ጊዜና ጥራት ለማጠናቀቅ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- FBC (Fana Broadcasting Corporate S.C.)
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.