Fana: At a Speed of Life!

የመዲናዋን ሰላም ለማስቀጠል እየተካሄደ ያለው የተቀናጀ ኦፕሬሽን ከፍተኛ ውጤት እያስመዘገበ መሆኑ ተጠቆመ

አዲስ አበባ፣ ጥር 30፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባን ሰላምና ደኅንነት አጠናክሮ ለማስቀጠል እየተካሄደ ያለው የፌደራልና የአዲስ አበባ ፖሊስ የተቀናጀ ኦፕሬሽን ከፍተኛ ውጤት እያስመዘገበ መሆኑን ፖሊስ አስታውቋል፡፡

ፖሊስ በሰጠው መግለጫ የአዲስ አበባን ሰላምና ደኅንነት አጠናክሮ ለማስቀጠል በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል የሚመራው የፌደራልና የአዲስ አበባ ፖሊስ የተቀናጀ ኦፕሬሽን ከፍተኛ ውጤት እያስመዘገበ መሆኑን አስታውቋል።

ጥምር አካላቱ ባካሄዱት ግምገማ በአዲስ አበባ ከተማ ሕዝብን ያማረሩ ወንጀሎች በከፍተኛ ደረጃ እየቀነሱ መምጣታቸውንና ለተሰራው የፀጥታ ሥራ ኅብረተሰቡ ዕውቅና እየሰጠ እንደሚገኝ በመግለጫው ተመላክቷል።

ከታህሳስ ወር 2016 ዓ.ም ጀምሮ ሳይቆራረጥ በጥብቅ ዲሲፒሊን እየተመራ ውጤቱም በየጊዜው ለህብረተሰቡ እየተገለፀ በኦፕሬሽኑ የተገኙ ውጤቶች፣ ያጋጠሙ ችግሮችና የተወሰዱ የማስተካከያ ዕርምጃዎች በግምገማው ላይ የተነሱ መሆኑን መግለጫው ጠቁሟል።

እንደመግለጫው በ7ኛው ዙር ከጥር 17 እስከ 29 ቀን 2016 ዓ.ም በተካሄደው ኦፕሬሽን የተገኙ ውጤቶች፦

የሀገር መከላከያ ሠራዊት በየአካባቢው በሸኔ የሽብር ቡድንና በፅንፈኛ ኃይሎች ላይ እያካሄደ ባለው ኦፕሬሽን ሸሽተው በሸገር ከተማ እና በአዲስ አበባ ከተማ የተሸሸጉ 37 የሸኔ እና 16 የፅንፈኛው ቡድን አባላት ከተለያዩ ከደበቋቸው የጦር መሣሪያዎች፣ ትጥቆችና ሚስጥራዊ ሰነዶች ጋር በአጠቃላይ 53 ፀረ-ሰላም ኃይሎች በቁጥጥር ሥር ውለዋል፡፡

የፀጥታ አካላት ሳይሆኑ የደንብ ልብስ ለብሰው ወንጀል ሲፈፅሙ የነበሩ 28 ተጠርጣሪዎች፣ በአዲስ አበባ ከተማ በተደረገ ጥብቅ ፍተሻ 14 ሕገ-ወጥ ክላሽንኮቭ ጠመንጀ ከመሰል 1 ሺህ 500 ጥይቶችና 5 ካርታ ጋር፣ 15 ልዩ ልዩ ሽጉጦች ከ158 መሰል ጥይት ጋር፣ የተለያዩ 383 የመኪና መለዋወጫዎች፣ ከፋይናንስ ሕጉ በተቃረነ ሁኔታ በሕገ-ወጥ መንገድ ተከማችቶ የተገኘ 28 ሺህ 5 መቶ 42 የአሜሪካ ዶላር፣ 34 ሺህ 400 ዮሮ፣ 34 ሺህ 155 የካናዳ ዶላር፣ 1ሚሊየን 8 መቶ 35 ሺህ 410 ብር፣ 1ሚሊየን 150 ሺህ የሶማሌ ላንድ ገንዘብ እና በርካታ የተለያዩ ሀገራት ገንዘቦች ከነ-ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራው መቀጠሉን ከመግለጫው መረዳት ተችሏል፡፡

በተመሳሳይ 1ሺህ 191 የተለያዩ የሞባይል ስልኮች፣ 24 ላፕቶፕ፣ 5 ቴሌቪዥን፣ 6 ታብሌቶች፣ 4 የጠረጴዛ ኮምፒዩውተር፣ በርካታ ሐሰተኛ ሰነዶች፣ የሺሻ ዕቃዎች፣ አደገኛ ዕፅ እና አዘዋዋሪዎች እንዲሁም የተሰረቀ ዕቃ የሚገዙ፤ የሚደልሉ ዋና ወንጀል ፈፃሚዎችን ጨምሮ በሕገ-ወጥ ተግባር ላይ ተሳትፎ የነበራቸው ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ውለዋል ብሏል መግለጫው።

ከዚህም ባሻገር ከወንጀል ፈፃሚዎች ጋር በመመሳጠር የፖሊስን መረጃ ለተጠርጣሪዎች አሳልፈው ሲሰጡ የነበሩና በሌሎች ጥፋቶች ላይ የተገኙ 146 የፖሊስ አመራሮችና አባላት ላይ አስተማሪ እርምጃ መወሰዱን መግለጫው አስታውቋል፡፡

የአትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል ፥ ወንጀልን ለመከላከል የሚደረገው ቁጥጥር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል መግለጻቸውን ከአዲስ አበባ ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

አክለውም 37ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ በሰላም እንዲጠናቀቅ ሁሉም የፀጥታና ደኅንነት አካላት ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ የሥራ መመሪያ በመስጠት ኅብረተሰቡም የተለመደውን ትብብር አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ማቅረባቸውን መግለጫው አንስቷል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.