Fana: At a Speed of Life!

ለኮንስትራክሽንና ለጭነት ተሽከርካሪዎች የተከለከሉ መንገዶች ይፋ ሆኑ

 

አዲስ አበባ፣ የካቲት 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ለአፍሪካ ህብረት መሪዎች ጉባዔ የትራፊክ ፍሠት የተሳለጠ ለማድረግ እንዲቻል ለኮንስትራክሽን እና ለጭነት ተሽከርካሪዎች የተከለከሉ መንገዶችን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ።

የኮንስትራክሽ ተሽከርካሪዎች እና በኦፕሬተር የሚንቀሳቀሱ ማሽኖች ጎማዎቻቸው ሳያፀዱ መንገዶችን ከማበላሸታቸው ባሻገር ለረጅም ጊዜ በመንገዶቹ ላይ በመቆም እና የሚጭኑትን አሽዋ ፣የቦካ ሲሚንቶ እንዲሁም የግንባታ ግብአቶችን በአግባቡ ሳያስሩ እና ሳይሸፍኑ እያፈሰሱ በመጓዝ በሚፈፅሙት የደንብ መተላለፍ ጥሰት የመንገዶቹ ውበት እየተበላሸ እና የአገልግሎት ዕድሜያቸው እያጠረ መምጣቱን የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅሷል፡፡

በመሆኑም የትራፊክ ህግና ደንብን በማስከበር የመንገድ ላይ የትራፊክ አደጋን ከመከላከል ባሻገር ጤናማ የትራፊክ ፍሰት እንዲኖር እንዱሁም በመዲናዋ በቀጣይ ቀናት ለሚካሔደው የአፍሪካ ህብረት ጉባዔ የፀጥታ አካላት ለሚያከናውኑት የፀጥታ ስራ አመቺ ሁኔታን መፍጠር እንዲቻል ከዚህ በታች በተገለፁት መንገዶች ማለትም፡-

• ቦሌ ድልድይ አካባቢ
• ከቦሌ ድልድይ እሰከ ሩዋንዳ ድልድይ
• ከቦሌ ድልድይ በወሎ ሰፈር ደንበል አደባባይ እስከ መስቀል አደባባይ
• ከመስቀል አደባባይ እስከ አራት ኪሎ
• ከኡራኤል አደባባይ እስከ አትላስ ሆቴል
• ከኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል እስከ ልማት ባንክ
• ከአራት ኪሎ እስከ አምባሳደር መናፈሻ
• ከብሄራዊ ቴአትር እስከ ሜክሲኮ አደባባይ
• ከሜክሲኮ አደባባይ እስከ አፍሪካ ህብረት ትራፊክ መብራት እና
• ከአፍሪካ ህብረት ትራፊክ መብራት እስከ ቡልጋሪያ ማዞሪያ ባሉት መንገዶች ላይ ተለዋጭ መረጃ እስኪተላለፍ ድረስ የኮንስትራክሽን ከባድ እና የጭነት ተሽከርካሪንዎችን ማሽከርከርም ሆነ ማቆም የተከለከለ መሆኑን ገልጿል፡፡ በዚህም አሽከርካሪዎች ሌሎች አማራጭ መንገዶችን እንዲጠቀሙ የአዲስ አበባ ፖሊስ ያሳሰበ ሲሆን÷ ይህንን ተላልፈው በተገኙት ላይ አስፈላጊውን እርምጃ እንደሚወስድ አስታውቋል፡፡

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.