Fana: At a Speed of Life!

የኮይሻ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት 3 ነጥብ 25 ሚሊየን ሜትር ኪዩብ የኮንክሪት ሙሊት ሥራ መከናወኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 12፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኮይሻ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት 3 ነጥብ 25 ሚሊየን ሜትር ኪዩብ የኮንክሪት ሙሊት ሥራ መከናወኑን የፕሮጀክቱ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ገለጹ።

ፕሮጀክቱን በተያዘለት ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑን የተናገሩት የፕሮጀክቱ ምክትል ሥራ አስኪያጅ አባይነህ ጌትነት÷ የዋና ግድብ፣ የኃይል ማመንጫ ቤቶች፣ የውሃ ማስተንፈሻና ሌሎች ተጓዳኝ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል፡፡

የግድብ ግንባታው 6 ነጥብ 6 ሚሊየን ሜትር ኪዩብ የአፈር ቁፋሮ በማካሄድ አጠቃላይ ግድቡ ከሚፈልገው 7 ነጥብ 7 ሚሊየን ሜትር ኪዩብ የኮንክሪት ሙሊት ውስጥ 42 በመቶው ማለትም 3 ነጥብ 25 ሚሊየን ሜትር ኪዩብ የኮንክሪት ሙሊት ሥራ መከናወኑን ተናግረዋል።

የኃይል ማመንጫው 2 ሚሊየን ሜትር ኪዩብ ቁፋሮ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ከሚያስፈልገው 160 ሺህ ሜትር ኪዩብ ኮንክሪት ሙሊት ውስጥ 52 በመቶው መከናወኑን ምክትል ሥራ አስኪያጁ ጠቁመዋል።

6 ነጥብ 65 ሚሊየን ሜትር ኪዩብ ቁፉሮ የሚጠይቀው የውሃ ማስተንፈሻ ሥራ 90 ከመቶው መጠናቀቁንና 13 በመቶ የሚሆን የአርማታ ሙሊት ሥራ መከናወኑንም አብራርተዋል።

በፋይናንስ በተለይም በውጭ ምንዛሬ እጥረት እና ተያያዥ ችግሮች ምክንያት ግንባታው በታቀደለት የጊዜ ገደብ እንዳይጠናቀቅ አድርጎት መቆየቱን ተናግረዋል።

የቀድሞ ሳሊኒ የአሁኑ ዊ ቢዩልድ የኮይሻ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ስራ አስኪያጅ ዞፒስ በበኩላቸው÷ ከአሁን ቀደም በኢትዮጵያ ከገነቧቸው ግድቦች ልምድ በመውሰድ የኮይሻ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክትን የሲቪል ስራ በታቀደለት የጊዜ ገደብ ለማጠናቀቅ የሚያስችሉ የቅድመ ዝግጅት ተደርጎ ወደ ሥራ መግባታቸውን ገልጸዋል።

የገጠሙትን ችግሮች በመፍታት የፕሮጀክቱን የሲቪል ሥራ በተቻለ ፍጥነት በተያዘው መርሐ ግብር ለማከናወን እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው÷ አሁን ላይ አጠቃላይ የፕሮጀክቱ አፈጻጸም 62 በመቶ ላይ መድረሱን ተናግረዋል።

የኮይሻ የውኃ ኃይል ማመንጫ ሲጠናቀቅ እያንዳንዳቸው 300 ሜጋ ዋት የሚያመነጩ 6 ተርባይኖች የሚኖሩት ሲሆን በዓመት በአማካይ 6 ሺህ 340 ጊጋ ዋት ሰዓት ኃይል ያመነጫል ተብሎ እንደሚጠበቅ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.