Fana: At a Speed of Life!

የአማራ ክልል የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት ችግርን ለመፍታት እየሰራ መሆኑን አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 12፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት ላይ ያጋጠመውን ችግር ለመቅረፍ እየተሠራ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ፡፡

ቢሮው ባለፈው የምርት ዘመን የተፈጠረውን እጥረት በመቅረፍ በወቅቱ የአፈር ማዳበሪያ ለማቅረብ የሚያስችል የግምገማ መድረክ አዘጋጅቷል፡፡

የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ/ር) በዚሁ ጊዜ እንዳሉት ÷ 1 ነጥብ 1 ሚሊየን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ በሚቀጥሉት 20 ቀናት ለተለያዩ ዞኖች ለማሰራጨት እቅድ ተይዟል፡፡

የክልሉ መንግሥት ሕዝቡ፣ የጸጥታ አካላት እና ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች ተባብረው በመሥራት አቅርቦቱን ለማቀላጠፍ በትኩረት እየተሠራ እንደሆነ ተናግረዋል።

የክልሉ ምክትል ግብርና ቢሮ ኃላፊ አጀበ ስንሻው በበኩላቸው÷ የአፈር ማዳበሪያ እጥረትን ለመቅረፍና የሥርጭት ሥርዓቱ ላይ እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

በክልሉ ከ 5 ነጥብ 2 ሚሊየን በላይ አርሶ አደሮች የአፈር ማዳበሪያ እንደሚጠቀሙ የተገለጸ ሲሆን ከጊዜ ወደ ጊዜ የአፈር ማዳበሪያ ፍላጎት እየጨመረ መምጣቱም ተነስቷል።

በተያዘው የ2016/17 የምርት ዘመን ለአማራ ክልል ብቻ 8 ሚሊየን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ የግዥ ውል የተያዘ ሲሆን ከባለፈው ዓመት ሲነጻጸር የ 3 ነጥብ 2 ሚሊየን ኩንታል ጭማሬ እንዳለው ተገልጿል።

ግዥ ከተፈጸመለት የአፈር ማዳበሪያ የአማራ ክልል ድርሻ 3 ነጥብ 5 ሚሊየን ኩንታል ወደብ ላይ መድረሱም ተነስቷል።

የአፈር ማዳበሪያውን በማሠራጨት ሂደት የጸጥታው ችግር እንቅፋት እንደሆነ በውይይቱ የተነሳ ሲሆን የፌዴራልና የክልሉና የፀጥታ አካላት ከትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች ጋር በመሆን አቅርቦቱን ለማሻሻል እየተሠራ መሆኑም ተገልጿል።

በደሳለኝ ቢራራ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.