Fana: At a Speed of Life!

በአቶ አባተ አበበ የግድያ ወንጀል የተጠረጠረው ተስፋዬ ሆርዶፋ ላይ የክስ መመስረቻ ጊዜ ተፈቀደ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት አራዳ ምድብ 1ኛ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት በአቶ አባተ አበበ የግድያ ወንጀል የተጠረጠረው ተስፋዬ ሆርዶፋ ላይ የክስ መመስረቻ ጊዜ ለዐቃቤ ሕግ ፈቀደ።

ተጠርጣሪው ተስፋዬ ሆርዶፋ በታህሳስ 7 ቀን 2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ቦሌ ኤድናሞል አካባቢ ከምሽቱ 4:00 ላይ አባተ አበበ የተባለ ግለሰብን በ3 ጥይት በመምታት ህይወቱ እንዲያልፍ አድርጓል ተብሎ በፖሊስ ተጠርጥሮ በቁጥጥር ስር ውሎ ምርመራ ሲጣራበት ቆይቷል።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን መርማሪ በተሰጠው የ11 የምርመራ ማጣሪያ ጊዜ ውስጥ ስራውን አጠናቆ መዝገቡን ለዐቃቤ ሕግ ማስረከቡን በዛሬው ቀጠሮ ለችሎቱ አስታውቋል።

የፍትህ ሚኒስቴር የልዩ ልዩ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጀነራል ዐቃቤ ሕግ የምርመራ መዝገቡን ከፖሊስ መረከቡን ገልጾ፤ መዝገቡን ተመልክቶ ለመወሰን እንዲያስችለው በወ/መ/ስ/ህ ቁጥር 109 ንዑስ ቁጥር 1 መሰረት የ15 ቀናት የክስ የመመስረቻ ጊዜ እንዲፈቀድለት ችሎቱን ጠይቋል።

የተጠርጣሪ ጠበቃ በበኩላቸው ደንበኛቸው ሁለት ወር ከስምንት ቀናት በእስራት ላይ መቆየታቸውን ጠቁመው፤ ፖሊስ ምርመራ ሲያከናውን በቆየበት ጊዜ ሁሉ ዐቃቤ ሕግ ምርመራውን እየመራ መቆየቱንና የቅድመ ምርመራ መዝገብም ማስከፈቱን ለችሎቱ ገልጸዋል።

በተጨማሪም የተጠርጣሪ ጠበቃ “ዐቃቤ ሕግ ምርመራውን ሲመራ በቆየበት መዝገብ ላይ እንደ አዲስ መዝገቡን ለመመልከትና ለመወሰን በሚል ክስ የመመስረቻ ጊዜ መጠየቁ አግባብ አይደለም” በማለት የመከራክሪያ ነጥብ አንስተዋል።

ከ3 ቀናት በላይ ለዓቃቤ ሕግ ክስ የመመስረቻ ጊዜ ሊሰጥ አይገባም በማለትም ተከራክረዋል።

ዐቃቤ ሕግ በበኩሉ “ምርመራው ላይ መመሪያ እንሰጣለን ማለት በእያንዳንዱ የምርመራ መዝገብ አብረን የምስክር ቃል እንቀበላለን፣ ማስረጃውንም እናውቃለን ማለት አይደለም” ሲል መልስ በመስጠት የጠየቀው የክስ መመስረቻ ጊዜ እንዲፈቀድለት በድጋሚ ጠይቋል።

የግራ ቀኝ ክርክሩን የተከታተለው ጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ ዐቃቤ ሕግ ከጠየቀው 15 ቀናት ውስጥ 10 ቀናት የክስ መመስረቻ ጊዜ ፈቅዷል።

ፍርድ ቤቱ ተጠርጣሪው ክስ እስኪመሰረትበት ድረስ ባለበት የፖሊስ ማቆያ እንዲቆይ በማለት ዐቃቤ ሕግ በተሰጠው ጊዜ ውስጥ ክስ የማይመሰርት ከሆነ አካልን ነጻ የማውጣት መብታችውን መጠየቅ እንደሚችሉ ገልጿል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.