15ኛው ከተማ አቀፍ የኪነ-ጥበብ ፌስቲቫል እየተካሄደ ነው
አዲስ አበባ፣ የካቲት 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) 15ኛው ከተማ አቀፍ የኪነ-ጥበብ ፌስቲቫል በጊዮን ሆቴል በይፋ ተከፍቷል፡፡
ፌስቲቫሉ ”ኢትዮጵያዊነት የሥነ-ጥበብ ምናብ ሠረገላ ፣ የወል ትርክት አለላ” በሚል መሪ ቃል ነው እየተካሄደ የሚገኘው።
በፌስቲቫሉ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ፣ ታላላቅ የጥበብ ባለሙያዎች ፣ ታዋቂ ሰዎች ፣ወጣትና ህፃናት የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎችን ጨምሮ በርካታ የማህበረሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል፡፡
በፌስቲቫሉ የተለያዩ የኪነ-ጥበብ ስራዎች ለህዝብ ዕይታ እየቀረቡ ነው።
የአዲስ አበባ ባህል ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ሂሩት ካሳው (ዶ/ር) በዚሁ ጊዜ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት ÷ብዝሃነታችንን ጠብቀንና አክብረን ኢትዮጵያዊነትን ከፍ ለማድረግ የኪነጥበብን ሚና መጠቀም ይኖርብናል ብለዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ ለኪነ ጥበብ ዘርፉ የመሰረተ ልማት ግንባታዎችን በማካሄድ የኢትዮጵያዊነት ልዕልና በኪነ- ጥበቡ እንዲንፀባረቅ እየተሰራ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
ፌስቲቫሉ ከዛሬ ጀምሮ ለሶስት ተከታታይ ቀናት እንደሚካሄድም ተጠቁሟል፡፡
በመለሰ ምትኩ