Fana: At a Speed of Life!

በመነጋገር ለችግሮች መፍትሔ ማምጣት የመንግሥት ጽኑ አቋም ነው – አቶ ብናልፍ አንዷለም

አዲስ አበባ፣ የካቲት 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ቁጭ ብሎ በመነጋገር ለችግሮች መፍትሔ ማምጣት የመንግሥት ጽኑ አቋም ነው ሲሉ የሰላም ሚኒስትር ብናልፍ አንዷለም ገለጹ።

በጋምቤላ ከተማ እየተካሄደ ባለው 6ኛው ሀገር አቀፍ የሰላምና የጸጥታ የጋራ የምክክር መድረክ ላይ የሰላም ሚኒስትሩ እንዳሉት÷ የሰላም ሥራ የሁሉንም አካላት ርብርብ እና ጥረት የሚጠይቅ ነው።

በኢትዮጵያ የተለያዩ ግጭቶች መከሰታቸውን ጠቁመው÷ ከእነዚህ የግጭት አዙሪቶች እና ከደረሱ ጉዳቶች ትምህርት በመውሰድ ለሰላም አማራጭ ቅድሚያ መስጠት እንደሚያስፈልግ አንስተዋል።

ማንኛውም ጥያቄ ያለው አካል በሰላማዊ መንገድ ቁጭ ብሎ በመነጋገር ለብዙ ችግሮች መፍትሔ ማምጣት ይቻላል ያሉት ሚኒስትሩ÷ ይህም የመንግሥት ጽኑ አቋም መሆኑን ተናግረዋል።

የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኡሞድ ኡጁሉ በበኩላቸው÷ ሰላም በተናጠል የሚመጣ ሳይሆን በተቀናጀ እና አንድነትን ባጠናከረ መንገድ የሚገኝ ነው ብለዋል።

ክልሉ ካጋጠመው ችግር ተላቆ ወደ ዘላቂ ሰላም ለመመለስ እየተደረገ ባለው የጋራ ጥረት ውስጥ የሁሉም አካላት ርብርብ መጠናከር እንዳለበት አስገንዝበዋል።

ክልሉ ቀደም ሲል በውስጥና በውጭ በሚከሰቱ ግጭቶች ተጎድቶ መቆየቱን አስታውሰው÷ የምክክር መድረኩ በጋምቤላ መካሄዱ አስተዋፅኦው የጎላ እንደሚሆን ተናግረዋል።

በቀጣይም አስተማማኝ ሰላምና ፀጥታ በማስፈን የተጀመሩ የልማት ስራዎችን አጠናክሮ ለማስቀጠል በትኩረት እንደሚሰራ ማረጋገጣቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.