በህዝቡ ስቃይ የሚሰራ የትኛውም ፖለቲካ ውጤቱ ምንም መሆኑን መረዳት ይገባል – የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን
አዲስ አበባ፣ የካቲት 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በህዝቡ ስቃይ የሚሰራ የትኛውም ፖለቲካ ውጤቱ ምንም መሆኑን መረዳት ይገባል ሲል የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ገለጸ፡፡
ፅንፈኛው ቡድን አሁን ደግሞ ክልሉን ወደ ጨለማ ለመክተት አልሞ እየሰራ ይገኛል ሲልም አስታውቋል፡፡
ኮሚሽኑ በወቅታዊ አሁናዊ ጉዳይ የሰጠው መግለጫ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡-
በህዝቡ ስቃይ የሚሰራ የትኛውም ፖለቲካ ውጤቱ ምንም መሆኑን መረዳት ይገባል።
ፅንፈኛ አሁን ደግሞ ክልሉን ወደ ጨለማ ለመክተት አልሞ እየሰራ ይገኛል።
የአማራን ህዝብ በማሠቃየትና ችግር ውስጥ በማስገባት ድል ይገኛል በሚል የእውር ድንበር የትግል ስልት የሚከተለው ፅንፈኛና ዘራፊ ኃይል ህዝቡን ወደ ተወሳሰበ ስቃይ አስገብቶታል።
ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ ባለፈው የተፈጠረውን ክፍተት አስቀድሞ ለመፍታት መንግሰት ለአርሶ አደሩ የሚልከውን ማዳበሪያ እንዳይደርስ ጉዞውን እያያስተጓጎለና እየዘረፈ ስለመሆኑ ሁሉም የሚያውቀው የእለት ተዕለት ተግብሩ ሆኗል።
በስንት ትግል ከአርሶ አደሩ ደጅ የደረሰውን ማዳበሪያ ደግሞ በነፃ ስለምትወስዱ ከመንግስት አትውሰዱ በሚል የሀሰት ፕሮፖጋንዳ በማሰራጨት ከፍተኛ ብጥብጥና ፍጅት ለመፍጠር ሙከራዎችን በተለያዩ አካባቢዎች እየፈጠረ ይገኛል።
ህዝብን ከቀን ወደ ቀን ወደ ተወሳሰበ ችግር ለመክተት አልሞ እየሰራ ያለው ፅንፈኛ ዘራፊ ቡድኑ በለመደው መንገድ በየካቲት 26 ቀን 2016 ዓ.ም እኩለ ቀን አካባቢ ከባህር ዳር – ደብረታቦር – ንፋስ መውጫ – ጋሸና – አላማጣ የተዘረጋው ባለ 230 ኪሎ ቮልት የከፍተኛ ኃይል ማስተላለፊያ መስመር በንፋስ መውጫ አካባቢ አንደኛው ፌዝ በመሳሪያ በመምታቱ ከሠዓት በኋላ ጀምሮ አብዛኛው የአማራ ክልል አካባቢ የመብራት አገልግሎት እንዲያጣ አድርጎታል።
ህዝባችን በቅጡ ያልተሟሉለት በርካታ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ችግሮች ሳይፈቱ በእንቅርት ላይ ጀሮ ደግፍ እንዲሉ የእለት ከእለት ህይወት በመብራት ላይ የተመሠረተውን ህዝብ ወደ ሌላ የጨለማ ምዕራፍ ጎትቶ በማስገባት የስቃይ ዓይነቶችን እየፈለገ ሲተገብር መዋሉ የቀን ተቀን ተግባሩ ሆኗል።
ይልቅ ህዝብን እንዲማረር በማድረግ ለትግል የማነሳሳት ዘዴ ያረጀ ያፈጀና ያለፈበትና የተነቃበት የትግል ስልት መሆኑን አልተረዳውም።
የህዝብን ኑሮ በማጎሳቆልና ወደ ድህነት በማስገባት የሚገኝ ድል አይገኝም ቢገኝም እንኳ የትም አያደርስም።
በቀጣይም የህዝብን ስቃይና ምሬት የሚጨምሩ ተግባራትን በመፈፀም መንግስት እንዲህ አደረገ ለማለት በዝግጅት ላይ እንዳለ መረጃዎች ያሳያሉ።
ስለሆነም ሠላም ወዳዱ ህዝባችን መሰል ድርጊቶችን ሲያይ ለክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን በስልክ ቁጥር 058-220-13-27 ሪፖርት እንዲያደርግ እና መላው የክልላችን ህዝብ በውድ የተዘረጋ የህዝብ ሀብት በዘራፊ ቡድኑ የሚደርስበትን ጥቃት ከፀጥታ ኃይሉ ጋር በመሆን መከላከል እንደሚገባ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ያሳውቃል!!!
የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን
የካቲት 26ቀን 2016 ዓ.ም
ባህርዳር