Fana: At a Speed of Life!

በሀገር ውስጥና በውጪ የሥራ ስምሪት ለ1 ነጥብ 4 ሚሊየን ዜጎች የሥራ ዕድል ተፈጠረ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 28፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለፉት ስድስት ወራት በሀገር ውስጥና በውጪ ሀገር የሥራ ስምሪት ለ1 ነጥብ 4 ሚሊየን ዜጎች የሥራ ዕድል መፈጠሩን የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የሥራ እና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል÷ባለፉት ስድስት ወራት ሪፎርሞችን ወደ ተሟላ ተግባር የመቀየር ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉን አንስተዋል፡፡

ስርዓት የመገንባት እና የሥራ እድል ፈጠራው ጥራት እንዳይኖረው ያደረጉ ማነቆዎችን መፍታት የሚያስችሉ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ በትኩረት መሰራቱንም ተናግረዋል፡፡

በዚህም በ6 ወራት ውስጥ 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ዜጎችን በአጫጭር ስልጠና ተደራሽ ለማድረግ ታቅዶ 1 ነጥብ 2 ሚሊየን ዜጎችን ተደራሽ ማድረግ ተችሏል ነው ያሉት፡፡

በሌላ በኩል ባለፉት ስድስት ወራት በሀገር ውስጥና በውጪ የሥራ ስምሪት 1 ነጥብ 4 ሚሊየን ዜጎች የሥራ ዕድል መፈጠሩን አንስተዋል፡፡

ከዚህም ውስጥ በሰባት ወር 230 ሺህ የሰለጠሉ ዜጎችን ለውጪ ሀገር የሥራ ስምሪት ልከናል ያሉት ሚኒስትሯ÷ ሲላኩም ክህሎት ያላቸው ዜጎች እንዲሄዱ ለማድረግ የሚያስችል ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል፡፡

ለውጪ ሀገር የሥራ ስምሪት ከሀገራት ጋር ስምምነቶችን ተፈራርመናል ያሉ ሲሆን÷ በስድስት ወር ውስጥ አዳዲስ መዳረሻዎች ላይ ሥራ ሰርተናል፤ ሁለት አዳዲስ ስምምነቶችንም ተፈራርመናል ብለዋል፡፡

በሒደት ላይ ያሉ አራት ስምምነቶች እንዳሉ የጠቆሙት ወ/ሮ ሙፈሪሃት÷ ይህም አዳዲስ መዳረሻዎችን እንድናገኝ እድል ይፈጥራል ነው ያሉት፡፡

መላክ ብቻ ሳይሆን ዘላቂነት ያለው የስርዓት ግንባታ እየተካሄደ መሆኑን ጠቅሰው÷ ከውጭም ሆነ በሀገር ውስጥ ካሉ ባለድርሻ አካላት ጋር እየሰራን ነው፤ ማነቆዎችም እየተፈቱ ነው ብለዋል፡፡

በዚህም ሚኒስቴሩ ከተለያዩ ተቋማት ጋር እየተሰራ መሆኑን እና በሀገር ውስጥ አዲስ ወደ ሥራ የሚገቡ ዜጎችን የፋይናንስ ችግር ለመፍታት ከልማት ባንክ ጋር እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ኢንተርፕራይዞች ምርታቸውን ለማስተዋወቅ እንዲረዳቸው ዲጂታል ኢ-ኮሜርስ ሥርዓት ሲለማ ቆይቶ ወደ ሥራ ገብቷል ያሉት ሚኒስትሯ÷ 1 ሺህ ኢንተርፕራይዞችም በዚህ ስርዓት መጠቀም ጀምረዋል ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል ጥራት ያለው ምርት የሚያመርቱ ኢንተርፕራይዞች ምርታቸውን የሚሸጡባቸው ቦታዎች ግንባታ በመከናወን ላይ እንደሆነ አመላክተዋል፡፡

በፌቨን ቢሻው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.