Fana: At a Speed of Life!

መንግሥት የዋጋ ግሽበትን ለማረጋጋት የተናበበ የፖሊሲ እርምጃ እየወሰደ መሆኑ ተመላከተ

 

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) መንግሥት የዋጋ ግሽበትን ለማረጋጋት የተናበበ የገንዘብ፣ የፊስካልና የምርታማነት የፖሊሲ እርምጃዎችን እየወሰደ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ገለጹ።

ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) እንዳሉት÷ የ2016 በጀት ዓመት ዕቅድና በጀት ይፋ ሲደረግ የዋጋ ግሽበትን በመቆጣጠር የኑሮ ውድነትን ማረጋጋት አንዱ የትኩረት መስክ ነው።

ለዚህም በፊስካል ፖሊሲ ደረጃ ለዓመቱ የዘርፍ ተቋማት የተመደበው በጀት በአንጻራዊነት ካለፈው ዓመት ብዙም ጭማሪ ያልተደረገበትና የዋጋ ግሽበትን ለማረጋጋት እንዲሰሩ የሚያስገድድ መሆኑን ይገልጻሉ።

በመሆኑም የገንዘብ ሚኒስቴር በበጀት ዓመቱ ቀሪ ወራትም የበጀት አሠራሩን ጠበቅ እንዲያደርግ በመንግሥት ተወስኖ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የዋጋ ግሽበቱን ለማረጋጋት የተናበበ የፖሊሲ እርምጃ እየተወሰደ ስለመሆኑ አብራርተው፤ ብሔራዊ ባንክም የገንዘብ ፖሊሲ ማሻሻያ በማድረግ ጥብቅ ውሳኔዎችን ማሳለፉን ጠቅሰዋል።

ለዚህም ብሔራዊ ባንክ መጠነ-ሰፊ የገንዘብ እንቅስቃሴን የሚያግድ እርምጃ እየወሰደ መሆኑን፣ የመንግሥትን የመበደር ምጣኔ መገደቡን፣ የባንኮችን የብድር እድገት ከ14 በመቶ እንዳያልፍ ማድረጉን ተናግረዋል።

ለመንግሥት የሚሰጠውን የቀጥታ የብድር መጠን በእጅጉ በመቀነስ ባለፈው ዓመት ከተሰጠው ብድር አንድ-ሦስተኛ እንዳይበልጥ እና መሠረታዊ በሆነ መልኩ እንዲገደብ ተደርጓል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ይህም ማለት የመንግሥት ወጪ እድገት እንዲገደብ፣ የበጀት ጉድለቱን ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት አኳያ እንዲቀንስ መደረጉን ተናግረዋል።

በምግብ ሸቀጦች ላይ ያለውን የዋጋ ግሽበት በዋናነት ለመፍታት ምርታማነትን ማሳደግና የንግድ ሥርዓቱን ማሻሻል ወሳኝ መሆኑንም ገልጸው፤ ለዚህም በሁለተኛው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራ ለምርት ማደግ፣ ለንግድ ሥርዓቱ ሪፎርም ትኩረት ተሰጥቷል ነው ያሉት።

በዘላቂነት የዋጋ ግሽበትን ለማረጋጋት የዜጎችን የመግዛት አቅም (ገቢ) የማሳደግ፣ የምርት ዋጋ ላይ ትርጉም ያለው ቅነሳ ማድረግ ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው፤ አሁንም ለውጦች አሉ ብለዋል።

ክልሎች ለምርታማነት ማደግና ለምርት ዝውውር በትብብር መሥራት እንዳለባቸው ገልጸው፤ የንግድ ቁጥጥር ተቋማት የምርት ግብይት ላይ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪን ሥርዓት በማስያዝ ለግሽበቱ መረጋጋት ሚናቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.