Fana: At a Speed of Life!

በአዲስ አስተሳሰብና እሳቤ ፈተናዎችን ወደ ዕድል በመቀየር የተረጋጋና ውጤታማ ጊዜያትን አሳልፈናል – አቶ ጥላሁን ከበደ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 4፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አስተሳሰብና እሳቤ ጸጋዎቻችንን ከመለየት እስከ ሀብት መፍጠር ፈተናዎችን ወደ ዕድል በመቀየር የተረጋጋና ውጤታማ ጊዜያትን አሳልፈናል ሲሉ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ገለጹ።

የክልሉ ምክር ቤት 6ኛ ዙር 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ጉባኤውን በአርባምንጭ ከተማ ማካሄድ ጀምሯል።

በጉባኤው የስድስት ወራት ዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት እያቀረቡ ያሉት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር፤ የክልሉ መንግስት ከምስረታ ማግስት ጀምሮ የሽግግር ጊዜ ዕቅድ በማዘጋጀት በተለይም ከህገ መንግስት መልስ ያሉ ህጎችን በማውጣት መደበኛ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎች ጊዜና ሃብትን ባገናዘበ መንገድ በብቃት መተግበራቸውን ገልጸዋል።

በዚህም ስድስቱንም የክልል ማዕከላት በማደራጀት በአዲስ አስተሳሰብና እሳቤ ጸጋዎቻችንን ከመለየት እስከ ሀብት መፍጠር ፈተናዎችን ወደ ዕድል በመቀየር የተረጋጋና ውጤታማ ጊዜ ማሳለፍ መቻሉን አብራርተዋል።

በከተማና በገጠር የሚሰሩ ስራዎች በተለይም የህዝብ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ያስችል ዘንድ የልማት ስራዎች መሰራታቸውንና የተለያዩ የአቅም ግንባታ ተግባራት መከናወናቸውን ተናግረዋል።

ከውስጥ ገቢ አብዛኛውን የወጪ ፍላጎት ትርጉም ባለው መንገድ በመሸፈን የተነገበውን ራዕይ ለማሳካት ከመላው ህዝብ ጋር መሰራቱን ገልጸዋል።

የገዢ ትርክትን በማስረጽ ከምንም በላይ ትርጉም ባለው መንገድ ክልላችን የመቻቻል ተምሳሌት መሆኑን ማረጋገጫ የሚሆን ተግባራትና የህዝብ ለህዝብ ትስስርን የማጠናከር ስኬታማ ስራዎች ተከናውነዋል ብለዋል።

የክለሉ ምክር ቤት ዋና አፈጉባኤ ወ/ሮ ፀሐይ ወራሳ በበኩላቸው በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዘላቂ ሰላምና አንድነትን ይበልጥ ለማጠናከር እንዲሁም ሙሰና እና ብልሹ አሰራርን ለመከላከል የኦዲት ግብረኃይል በማደራጀት በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ክልሉ አዲስ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የምክር ቤት አባላት አሰራርና ደንብ እንዲያውቁም የተለያዩ ስልጠናዎች እየተሰጡ ይገኛሉ ብለዋል።

የክልሉ ህዝብ አብሮትና አንድነትን ይበልጥ በማጠናከር በልማት ስራ ላይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን በመግለጽ የሚነሱ ጥያቄዎችም እንዲመለሱ እየተሰራ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

በሌላ በኩል ክልሉ የአደረጃጀት ለውጥ ካካሄደ በኋላ ያከናወናቸውን የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎች የፎቶ ኤግዚቢሽን ለክልሉ ምክር ቤት አባላት ለጉብኝት ክፍት ሆኗል።

ኤግዚቢሽኑን መርቀው የከፈቱት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ እና የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ጸሐይ ወራሳ ሲሆኑ÷የኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሰናይት ሰለሞን አጠቃላይ የኤግዚቢሽኑን ይዘት ለክልሉ ምክር ቤት አባላት አስጎብኝተዋል።

በማቴዎስ ፈለቀ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.