Fana: At a Speed of Life!

ጎረቤት ሀገራት ለሚጠይቁት የኤሌክትሪክ ሃይል ምላሽ ለመስጠት ዝግጅት መደረጉ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 6፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የጎረቤት ሀገራት ለሚጠይቁት ተጨማሪ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ምላሽ ለመስጠት ዝግጅት መደረጉን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የውኃና ኢነርጂ ሚኒስትር ሃብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር ኢ/ር) እንደገለጹት÷ ኢትዮጵያ ያላትን የተፈጥሮ ጸጋ ተጠቅማ በምታመነጨው የኤሌክትሪክ ሃይል ሀገራት የሃይል ግዥ ለመፈጸም ከፍተኛ ፍላጎት እያሳዩ ነው።

በዚህም ጅቡቲ፣ ሱዳን እና ኬንያ ከኢትዮጵያ ጋር በሃይል መተሳሰራቸውን ነው የተናገሩት፡፡

ከኬንያ ጋር የተደረገው የሃይል ትስስር እስከ ታንዛኒያን እንዲሁም ደቡብ አፍሪካን ጭምር የሚያስተሳስር መሆኑን ጠቁመዋል።

በዚህም ኢትዮጵያ ቀጣናውን በኤሌክትሪክ ሃይል በማስተሳሰር ትልቅን ድርሻ እየተወጣች መሆኑን ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ እያቀረበች ያለው የኤሌክትሪክ ሃይል የሚመነጨው ከውሃ መሆኑና ይህም የአየር ንብረት ብከለት የማያስከትል መሆኑን ተፈላጊነቱ እንዲጨምር አድርጓል ብለዋል።

የሚቀርበው የኤሌክትሪክ ኃይል በዝቅተኛ ታሪፍ መሆኑም ተፈላጊነቱ እንዲጨምር ማስቻሉን እንደገለጹም ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ይህንንም ተከትሎ አሁን ላይ የጎረቤት ሀገራት የኤሌክትሪክ ሃይል ፍላጎት በየዓመቱ 15 በመቶ ጭማሪ እያሳየ መምጣቱን ነው ያስረዱት።

በቀጣይም የጎረቤት ሀገራት ለሚጠይቁት ተጨማሪ የኤሌክትሪክ ሃይል አቅርቦት ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል አቅም መፈጠሩን አመላክተዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.