Fana: At a Speed of Life!

በቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ አንዲትን መንገደኛ ወርቅና ብር ይዞ መውጣት አይቻልም በሚል ሙስናና እንግልት ፈጽሟል የተባለ ሰራተኛ በቁጥጥር ስር ዋለ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በቅርቡ በቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ አንዲትን መንገደኛ ወርቅና ብር ይዞ መውጣት አይቻልም በሚል ሙስናና እንግልት ፈጽሟል የተባለ ሰራተኛ በቁጥጥር ስር መዋሉን የኢትዮጵያ አየር መንገድ አስታወቀ፡፡

የአየር መንገዱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ጣሰው በሰጡት መግለጫ÷ በቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ውስጥ ለሚፈፀሙ ወንጀሎች አየር መንገዱን ሙሉ በሙሉ ተጠያቂ ማድረግ ተቀባይነት የለውም ብለዋል።

በአውሮፕላን ማረፊያ ውስጥ ከአየር መንገዱ በተጨማሪ፣ ኢሚግሬሽን፣ ጉምሩክ፣ ብሄራዊ መረጃና ደህንነት እንዲሁም ፌዴራል ፖሊስ የራሳቸው ድርሻ እንዳላቸው አስረድተዋል።

በቅርቡ በቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ አንዲትን መንገደኛ ወርቅና ብር ይዞ መውጣት አይቻልም በሚል ሙስናና እንግልት የፈጸመው አንድ የጉምሩክ ኮሚሽን ሰራተኛ እንጅ የአየር መንገዱ ሰራተኞች አይደሉም ብለዋል፡፡

ድርጊቱን በመፈጸም የተጠረጠረው የጉምሩክ ኮሚሽን ሰራተኛ በደህንነት ካሜራ እገዛ በቁጥጥር ስር መዋሉንም ነው ያረጋገጡት፡፡

በቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ውስጥ ከ3 ሺህ በላይ የደህንነት ካሜራዎች መኖራቸውንም አስገንዝበዋል፡፡

በአውሮፕላን ማረፊያ ውስጥ መሰል ድርጊቶች እንዳይፈፀሙ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅርበት እንደሚሰራ ተናግረዋል።

አሁን ላይ 145 አውሮፕላኖች አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን አንስተው÷ በቅርቡ የአዳዲስ አውሮፕላኖች ግዥ ትዕዛዝ መሰጠቱንም ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ በአየር ትራንስፖርት ዘርፍ እያሳየች ያለው የላቀ ውጤትና እመርታ ተጠናክሮ እንደሚቀጥም ነው ያረጋገጡት፡፡

በቅድስት ተስፋዬ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.