Fana: At a Speed of Life!

የባንኩን የሳይበር ደኅንነት አልፎ መግባት የቻለ አካል የለም-የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከውጭ የሚሰነዘርበትን የሳይበር ጥቃት የመቋቋም አቅም እንዳለው አስታወቀ፡፡

የባንኩ ፕሬዚዳንት አቤ ሳኖ በሰጡት መግለጫ÷ በርካታ የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች ቢሰነዘሩም በባንኩ የሳይበር ደኅንነት ላይ የደረሰ ችግር አለመኖሩን አረጋግጠዋል፡፡

ከሰሞኑ የተስተዋለው ችግርም የአገልግሎት ማሻሻያ ለማድረግ በነበረ ሥራ ምክንያት የተከሰተ ነው ብለዋል፡፡

የተፈጠረውን ችግር በመፍታት ሂደት የተደረሰበትን ደረጃም በቀጣይ ይፋ እናደርጋለን ነው ያሉት፡፡

አገልግሎቱ በጊዜው የጠፋውም ተጨማሪ ጉዳት እንዳይደርስ እንጂ የሲስተሙ ችግር እንዳልሆነም ጠቅሰዋል፡፡

በወቅቱም ከ490 ሺህ በላይ ጤነኛ እና ሕጋዊ ያልሆነ ግብይት መከናወኑን ጠቅሰው÷ በዚህ ሂደትም የተዘዋወረ ገንዘብ ወጪ እንዳይሆን መታገዱን አንስተዋል፡፡

በዚህ ሂደት ውስጥ የተከናወኑ ግብይቶችን የመመርመር ሥራው መቀጠሉንና በተለይም ከፍተኛ ግብይት ያከናወኑትን ለጸጥታ አካላት ማሳወቅ መቻሉንም ጠቁመዋል፡፡

በዚህ ድርጊት ላይ የተሳተፉት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መሆናቸውን ያመላከቱት የባንኩ ፕሬዚዳንት÷ አሁን ላይ የስም ዝርዝራቸው መውጣቱን ተከትሎ ገንዘቡን እየመለሱ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

እስካሁን ያልመለሱ ተማሪዎችም ገንዘቡን እንዲመልሱ ጠይቀዋል፡፡

በይስማው አደራው እና አሸናፊ ሽብሩ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.