Fana: At a Speed of Life!

የጎንደር ከተማን ኢንቨስትመንት ለማሳደግ የተከናወኑ ተግባራት አበረታች መሆናቸው ተመላከተ

 

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የጎንደር ከተማን ኢንቨስትመንት ለማሳደግና የሌማት ትሩፋት መርሐ-ግብርን ለማሳካት የተከናወኑ ተግባራት አበረታች መሆናቸውን የፍትሕ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

በፍትሕ ሚኒስትሩ የተመራ የፌዴራል መንግስት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ልዑክ በጎንደር ከተማ የተከናወኑ የኢንቨስመንት፣ የሌማት ትሩፋት፣ የአረንጓዴ ዐሻራና የመሰረተ ልማት ግንባታዎችን ጎብኝቷል፡፡

በዚሁ ወቅት ሚኒስትሩ÷ ከተማ አሥተዳደሩ ሰላምን ከማስፈን በተጓዳኝ ያከናወናቸው የልማትና የመልካም አሥተዳደር ተግባራት የሚደነቁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የከተማው የኢንቨስትመንት ፍሰት እንዲጨምር የተከናወኑ ተግባራትም አምራች ኢንዱስትሪዎች እንዲስፋፉና የሀገሪቱ የወጪ ምርት እንዲጠናከር የሚያግዙ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል፡፡

ባለሀብቶችም ተግዳሮቶችን ተቋቁመው የዕለት ተዕለት ተግባራቸውን ለማከናወን እያደረጉት ያለው ጥረት የሚያበረታታ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ወጣቶችን የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ከማድረግ ባለፈ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ-ግብርና በሌሎች የልማት ሥራዎች አተገባበር አበረታች ውጤት መታየቱንም ነው ሚኒስትሩ የገለጹት፡፡

በተመሳሳይ በከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ የተመራ የፌዴራል መንግሥት የድጋፍና ክትትል ልዑክ በባሕር ዳር ከተማ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎችን ጎብኝቷል፡፡

ሚኒስትሯ በዚሁ ወቅት እንዳሉት÷ በመገንባት ላይ የሚገኙት የመንገድ መሠረተ ልማቶች የባሕርዳር ከተማን ውበት እና የወደፊት እድገት የሚመጥኑ ናቸው፡፡

ከተማዋን ዘመናዊ፣ መሰረተ ልማት የተሟላላት እና ለነዋሪዎቿ ምቹ ለማድረግ የተጀመረውን ጥረት አድንቀው÷ ሚኒስቴሩ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ለአሚኮ ተናግረዋል፡፡

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.