Fana: At a Speed of Life!

የዓድዋ ድል መታሰቢያ የሕዝብን ኅብረትና ትብብር ጠቀሜታን ያስተምራል

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የዓድዋ ድል መታሰቢያ የዓድዋን ታሪክ ለማወቅ ከማገዙ በዘለለ ሀገሪቱን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ የሕዝብ ኅብረት አስፈላጊነትን እንደሚያስተምር የእስልምና ኃይማኖት መምህራንና አባቶች ተናገሩ።

ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የመጡ የእስልምና ኃይማኖት መምህራንና የእምነቱ አባቶች የዓድዋ ድል መታሰቢያን ዛሬ ጎብኝተዋል።

በጉብኝቱ በኢትዮጵያ ትልቅ የታሪክ ኃብት ስለሆነው አድዋ ድል ያላቸውን መረጃ ሊያጎለብቱላቸው የሚችሉ መረጃዎችን ማግኘት እንደቻሉ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት ሼይኸ አብዱላዚዝ አብዱልዋሊ፤ የአድዋ ድል መታሰቢያ የኢትዮጵያውያንን ማንነት የሚገልጽ ጥልቅ የሀገር ኃብት ፕሮጀክት ነው ብለዋል።

መታሰቢያው ኢትዮጵያውያን በኅብረት የሀገሪቱን ሕልውና ለማስጠበቅ የከፈሉትን ዋጋ እንደሚያሳይ ገልጸው፤ እርስ በርስ ያለንን አንድነት ማጠናከር እንዳለብን ትምህርት ይሰጣልም ነው ያሉት።

በጠቅላይ ምክር ቤቱ የፕሬዚዳንቱ ልዩ አማካሪና የኃይማኖት መምህር ኡስታዝ አቡበከር አህመድ በበኩላቸው፤ መታሰቢያው የቀደሙ አባቶች የሀገሪቱን የግዛት አንድነት ለማስጠበቅ የከፈሉትን ዋጋ ይዘክራል ብለዋል።

ይህም በአንድነት ከቆምንና ተባብረን ከሠራን ሀገሪቱን ወደ ተሻለ ደረጃ ማድረስ እንደሚቻል ትምህርት መውሰድ የሚያስችል ፕሮጀክት መሆኑን ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ ብዙ ሊነገሩና መታሰቢያ ሊቆምላቸው የሚገቡ የትላልቅ ታሪኮች ባለቤት ናት ያሉት ደግሞ የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ሥራ አስፈጻሚ ኡስታዝ መሐመድ አባተ ናቸው።

የሀገሪቱን ታሪካዊ ኃብቶች የሚያሳዩ ሌሎች መታሰቢያዎች በተለያዩ አካባቢዎች ሊሰፉ እንደሚገባም መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.