Fana: At a Speed of Life!

አሜሪካ ኤችአይቪ/ኤድስን ለመግታት የ111 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ ለኢትዮጵያ ይፋ አደረገች

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የአስቸኳይ ጊዜ የኤድስ ድጋፍ ዕቅድ ኢትዮጵያ በፈረንጆቹ 2030 ኤችአይቪ/ኤድስን ለማጥፋት የምታደርገውን ጥረት ለመደገፍ የሚውል የ111 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ ይፋ አድርጓል።

የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የኤድስ አስተባባሪና የዓለም ጤና ጥበቃ እና የጤና ደህንነትና ዲፕሎማሲ ከፍተኛ ባለስልጣን አምባሳደር ዶ/ር ጆን ንኬንጋሶንግ ድጋፉ መፅደቁን ይፋ አድርገዋል፡፡

የኮፕ-23 2ኛ ዓመት ዕቅድ በአሜሪካ መንግስት የአስቸኳይ ጊዜ ዕቅድ እና በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር መካከል በኢትዮጵያ የኤችአይቪ ቫይረስ ተጠቂዎችን ለመደገፍ ያለውን ትብብር የሚወክል መሆኑ ተገልጿል።

በአምባሳደር ንኬንጋሶንግ ድጋፉ መፅደቁ ኢትዮጵያ ወረርሽኙን ለመቆጣጠር የሚያስችል መንገድ ላይ መሆኗን እንደሚያረጋግጥ ተመላክቷል፡፡

ፕሮግራሙ ከጤና ሚኒስቴርና ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር አካባቢያዊ ልዩነት ሳይኖር ቁልፍ የማህበረሰብ ክፍሎች ኤችአይቪ መከላከል፣ እንክብካቤ እና ህክምና ላይ ያለውን ክፍተት ማጥበብ ላይ ያተኮረ ዕቅድ መንደፋቸው ተገልጿል፡፡

ዕቅዱም በዋነኛነት ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች የኤችአይቪ አገልግሎትን ማሻሻል፣ ችግሮችን የመለያ ስልቶችን ማጎልበት ማለትም ለአደጋ ተጋላጭ የሆኑ እንደ ህጻናት፣ ታዳጊዎች እና ጾታን መሰረት ካደረገ ጥቃት የተረፉ ሰዎችን መድረስ ቅድሚያ ይሰጠዋል ተብሏል።

ፕሮግራሙ ባለፉት 21 ዓመታት ውስጥ ኢትዮጵያ ለኤችአይቪ የምትሰጠውን ምላሽ ሲደግፍ መቆየቱን ከአሜሪካ ኤምባሲ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

መዋዕለ ነዋዩም የጤና ስርዓቱን በሰው ሃይል ልማት በማጠናከር፣ የኤችአይቪ አገልግሎትን ለመደገፍ መሠረተ ልማቶችን በማሻሻል እና ሪፈራል ላቦራቶሪዎችን እና ብሔራዊ የጤና መረጃ ስርዓትን በመዘርጋት ድጋፍ ማድረጉም ተጠቁሟል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.