Fana: At a Speed of Life!

ኅብረቱ ጥቂት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ላይ የፈጸሙትን ድርጊት አወገዘ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 11፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ኅብረት ጥቂት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ላይ የፈፀሙትን ያልተገባ ድርጊት አወገዘ።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አሠራሩን ለማዘመን ባደረገው እንቅስቃሴ በተፈጠረ ስህተት የገንዘብ ልውውጥ የአንዳንድ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጥቂት ተማሪዎች መሳተፋቸውን ኅብረቱ ገልጿል፡፡

የኅብረቱ ፕሬዚዳንት ሚካኤል ያቦነሽ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ÷ በዚህ ድርጊት ላይ የተሳተፉ ተማሪዎች ተግባር በፍፁም ተቀባይነት የሌለውና የሚወገዝ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በመንግሥት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አሁን ላይ ከ1 ነጥብ 1 ሚሊየን በላይ ተማሪዎች መኖራቸውን ጠቁመው÷ የተፈፀመው ድርጊት ሁሉንም የማይወክል መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

በነበረው ሕገ-ወጥ እንቅስቃሴ በማያውቁት መንገድ ተሳታፊ የነበሩ ተማሪዎች እንደነበሩ አስታውሰው÷ የወሰዱትን ገንዘብ መመለሳቸውን ተናግረዋል፡፡

በዚሁ ተግባር ላይ ተሳትፈው የነበሩ ሌሎች ተማሪዎችም በወቅቱ የተመዘበረውን የሀገርና የሕዝብ ሀብት እየመለሱ መሆናቸውን ገልጸው÷ ገንዘቡን በማስመለስ ረገድ ኅብረቱ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር እየሠራ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.