Fana: At a Speed of Life!

የሰብዓዊ ድጋፎችን በፍትሃዊነት በማሰራጨት ረገድ ክልሎች ሃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ተጠየቀ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በመንግስት እየቀረቡ ያሉ ሰብዓዊ ድጋፎችን በፍትሃዊነት በማሰራጨት ረገድ ክልሎች ሃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን አሳሰበ።

በኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ተወካይ ሥራ አስፈጻሚ አታለል አቦሃይ÷በሰው ሠራሽና የተፈጥሮ አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች የዓይነትና የገንዘብ ድጋፍ በተጠናከረ መልኩ እየቀረበ ነው ብለዋል።

በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት በሦስት ዙሮች ጥሬ ግንዘብና አልሚ ምግቦችን ጨምሮ ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ሰብዓዊ ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች ተደራሽ መደረጉን ተናግረዋል።

በዚህም ከ894 ሺህ ኩንታል በላይ እህል እና 540 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር የጥሬ ገንዘብ ድጋፍ መደረጉን ነው ያስረዱት፡፡

በአንደኛ እና ሁለተኛ ዙር ለ7 ነጥብ 3 ሚሊየን ዜጎች የዓይነትና የጥሬ ገንዘብ ድጋፍ መደረጉን አስታውሰዋል።

በሦስተኛ ዙር ደግሞ ለ6 ነጥብ 5 ሚሊየን ዜጎች ሰብዓዊ ድጋፍ የቀረበ ሲሆን÷ በሦስቱም ዙሮች በአጠቃላይ የ15 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር የዓይነትና የጥሬ ገንዘብ ድጋፍ ተደርጓል ብለዋል።

የሰብዓዊ ድጋፉ በተፈጥሮና ሰው ሠራሽ ችግሮች ድጋፍ ለሚሹ የአፋር፣ ትግራይ እና አማራ ክልሎች ነዋሪዎች የቀረበ መሆኑን ጠቁመዋል።

መንግሥት ሰብዓዊ ድጋፍ አቋርጠው የወጡ ለጋሽ ድርጅቶች የፈጠሩትን ክፍተት ለመሙላት ከመጠባበቂያ የምግብ መጋዘኖች 894 ሺህ 302 ኩንታል እህል ድጋፍ ማቅረቡን ጠቅሰዋል።

ዓለም አቀፍ አጋር ድርጅቶች ሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦቱን አቋርጠው እንደነበር አስታውሰው÷በዲፕሎማሲያዊ ንግግር በመንግሥት መር አካሄድ ድጋፋቸውን እንዲቀጥሉ ማድረግ ተችሏል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና በኮሚሽኑ የሥራ ኃላፊዎች የዲፕሎማሲ ሥራ የዓለም የምግብ ፕሮግራምና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጥምረት በ3ኛው ዙር ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልፀዋል።

ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች በ3ኛው ዙር 30 በመቶ የሚሆን የ400 ሺህ ኩንታል የሰብዓዊ ድጋፍ መቅረቡን ጠቅሰው÷ ድጋፉ በ4ኛው ዙርም መቀጠሉን ተናግረዋል።

መንግሥት ዓለም አቀፍ ድርጅቶችን በማስተባበር በ4ኛው ዙር ለ6 ነጥብ 6 ሚሊየን ዜጎች ሰብዓዊ ድጋፍ እያቀረበ መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡

ስለሆነም የሚቀርቡ ድጋፎችን በፍትሃዊነት በማሠራጨት ረገድ ክልሎች ሃላፊነታቸውን በአግባቡ ሊወጡ እንደሚገባ ነው ያሳሰቡት፡፡

ዓለም አቀፍ ተቋማት፣ ለጋሽ ድርጅቶችና ባለሃብቶችም ሰብአዊ ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.