Fana: At a Speed of Life!

የመቀሌ ኢንዱስትሪ ፓርክ ዳግም ሥራ ጀመረ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የመቀሌ ኢንዱስትሪ ፓርክ ወደ ምርት ሒደት መመለሱን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን አስታውቋል፡፡

የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈፃሚ አክሊሉ ታደሰ እንደገለጹት÷ በሰሜኑ ግጭት ምክንያት ባለፉት ግዜያት ሥራ አቁሞ የቆየው የመቀሌ ኢንዱስትሪ ፓርክ በዛሬው ዕለት ወደ ሥራ ገብቷል፡፡

ፓርኩን ዳግም ሥራ ለማስጀመርም ኮርፖሬሽኑ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ በትብብር ሲሰራ መቆየቱን ነው የተናገሩት፡፡

በፊት በኢንዱስትሪ ፓርኩ ውስጥ ያመርቱ የነበሩ ኩባንያዎች ወደ ሥራ እንዲገቡና አዳዲስ ኢንቨስተሮች በፓርኩ ለማምረት ባቀረቡት ጥያቄ መሰረት የቅድመ ኢንቨስትመንት ሥራዎቻቸውን እያጠናቀቁ መሆኑን አንስተዋል፡፡

ኮርፖሬሽኑም ኩባንያዎቹ ዳግም ወደ ምርት ሒደት እንዲገቡ ከፍተኛ ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ አረጋግጠዋል።

ፓርኩ በሙሉ አቅሙ ወደ ምርት ሒደት እንዲገባና ምቹ የኢንቨስትመንት ከባቢ ለመፍጠር እየተደረጉ ያሉ ጥረቶችን ሌሎች ባለድርሻ አካላት እንዲደግፉም ጥሪ ማቅረባቸውን የኮርፖሬሽኑ መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.