Fana: At a Speed of Life!

በዋሽንግተን ዲሲ ሲካሄድ የነበረው የኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባ ተጠናቀቀ

አዲስ አበባ፣ህዳር 30፣2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በዩናይትድ ስቴትስ ዋሽንግተን ዲሲ ሲካሄድ የነበረው የኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባ ተጠናቀቀ።

በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ አተኩሮ በተካሄደው ስብሰባ ላይ የሀገራቱ የውሃ ሚኒስትሮችም የተካፈሉ ሲሆን፥ የአሜሪካ መንግስት እና የዓለም ባንክ ተወካዮችም በታዛቢነት ተሳትፍዋል።

ሚኒስትሮቹ በስብሰባቸው በውሃ ሚኒስትሮች ደረጃ የተካሄዱት የባለሙያዎች ስብሰባዎች ያመጡትን አወንታዊ ለውጦች ተመልክተዋል።

በቀጣይ የሚካሄዱ መሰል ሁለት ስብሰባዎችም በግደቡ የውሃ አሞላል እና አስተዳደር ላይ ህግና መመሪያ እንዲያዘጋጅ፣ የድርቅ ሁኔታዎች ተብለው የሚወሰዱትን እና ድርቅን ለመከላከል የሚወሰዱ እርምጃዎችንም ከወዲሁ ለማስቀመጥ ተስማምተዋል።

ሚኒስትሮቹ ህግ እና መመሪያ መዘጋጀቱ በቀጣይ የሚኖር የድርቅ ሁኔታን ለመከላከል እንደሚያስችል ነው ያሰመሩበት።

የግድቡን ውሃ አሞላል እና አስተዳደር በተመለከተ የሚዘጋጁት የቴክኒክ ህጎች እና መመሪያዎች በኢትዮጵያ የሚፈፀም ሲሆን፥በወቅቱ ያለው የዓየር ሁኔታ እየታየ ሶስቱ ሀገራት ተነጋግረው ይህን ህግ ሊያሻሽሉ እንደሚችሉም ተቀምጧል።

የሚደረስ ስምምነትን ለማጠናቀቅ በካርቱም እና አዲስ አበባ የሚካሄዱት ስብሰባዎች ውጤትንም ለመገምገም ሚኒስትሮቹ በፈረንጆቹ የፊታችን ጥር 13 ቀን 2020 በዋሽንግተን ለመገናኘትም ተስማምተዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.