Fana: At a Speed of Life!

ኮሚሽኑ በአማራ ክልል በሰብዓዊ መብት አያያዝ ላይ ድጋፍ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኑን ገለጸ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 18፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአማራ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽን የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና እና የአፍሪካ ኅብረት ዳይሬክተር ማርሴል አክፖቮ ጋር ተወያይተዋል።

አቶ አረጋ ከበደ÷ በሰሜኑ ጦርነት የደረሰውን ጉዳት ጨምሮ በክልሉ ባለፉት ዓመታት እና በአሁኑ ወቅት ያለውን የሰብዓዊ መብት አያያዝ በተመለከተ መወያያታቸውን ገልጸዋል።

አሁን ያለውን የአማራ ክልል ግጭት ያስከተለው ጉዳት በተመለከተ በዝርዝር መወያየታቸውን ጠቁመው÷ በአማራ ክልል በተከሰተው ድርቅ የሰብዓዊ ድጋፍ ማድረግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መክረናል ነው ያሉት።

ከክልሉ መንግሥት ጋር መሥራት በሚቻልባቸው ሁኔታዎች መወያየታቸውን ጠቅሰው÷ ሙያዊ እና የገንዘብ ድጋፍ ማድረግ በሚገባቸው ጉዳዮች ላይ መምከራቸውን ነው የተናገሩት።

ድርጅቱ ከአማራ ክልል አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ማሥተባበሪያ ኮሚሽን እና የአማራ ክልል መልሶ ማቋቋም ፈንድ ጽሕፈት ቤት ጋር አብሮ ለመሥራት ዝግጁ መሆኑን ገልጿል ብለዋል።

ተቋሙ በአማራ ክልል ካለው ሰፊ ችግር አንፃር የሚጠበቅበትን አለመሥራቱን ማስገንዘባቸውን ተናግረዋል።

ወደ ፊት በትኩረት እንደሚሠሩ ቃል ገብተዋል ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ÷ በየጊዜው በመገናኘት በሰብዓዊ አያያዝ እና ድጋፍ ዙሪያ ለመምከር መስማማታቸውንም አስታውቀዋል።

ርዕሰ መሥተዳድሩ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ተቋማት በአማራ ክልል የሰብዓዊ ድጋፍ እንዲያድርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

በአማራ ክልል በተፈጠረው የፀጥታ ችግር እና የሰብዓዊ አያያዝ ዙሪያ መወያየታቸውን የገለጹት ማርሴል አክፖቮ በበኩላቸው፤ ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ መፍታት እንደሚገባ ማንሳታቸውንና የግጭቱ ዋና ምክንያት በሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ መምከራቸውን አሚኮ ዘግቧል፡፡

የክልሉ መንግሥት የሰብዓዊ መብት ጥበቃ በተመለከተ ያለውን ተነሳሽነት አድንቀው፤ ድርጅታቸው ለሰብዓዊ መብት ጥብቃ ትኩረት እንደሚያደርግ አስረድተዋል፡፡

መንግሥት ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የሚያደርገውን ጥረት አድንቀው÷ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ላይ ተጠያቂነት እንዲኖር መምከራቸውንም ገልጸዋል።

ድርጅታቸው በሰብዓዊ መብት አያያዝ ላይ ድጋፍ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኑን እና በግጭቱ ንጹሃን ዜጎች ከየትኛውም አካል ከለላ ሊሰጣቸው እና መጠበቅ እንዳለባቸውም አመላክተዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.