Fana: At a Speed of Life!

ከ3 ቢሊየን ብር በላይ ያስመዘገቡ ኩባንያዎች የማዕድን ማምረት ፈቃድ ተሰጣቸው

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ከሶስት ቢሊየን ብር በላይ ኢንቨስትመንት ያስመዘገቡ አራት ኩባንያዎች የማዕድን ማምረት ፈቃድ እንደተሰጣቸው የማዕድን ሚኒስቴር አስታወቀ።

የፈቃድ ስምምነቱን የማዕድን ሚኒስትር ሀብታሙ ተገኘ (ኢ/ር) እና የኩባንያዎቹ ስራ አስፈጻሚዎች ተፈራርመዋል፡፡

ለኩባንያዎቹ ፈቃድ የተሰጠው የብሮሚን፣ የግራናይት፣ የድንጋይ ከሰል እና የደለል ወርቅ ማእድናትን ለማልማት በተወሰነው መሰረት መሆኑ ተገልጿል።

ኩባንያዎቹ የማዕድን ምርመራ ፈቃድ ወስደው የምርመራ ስራ በመስራት እና ከዚህ በፊት የተሰሩ ጥናቶችን መረጃ በመጠቀም ወደ ምርት ለመግባት የሚያስችል የቴክኒክና የፋይናስን መረጃዎችን አሟልተው በመገኘታቸው እንደሆነም ተነግሯል።

የማምረት ፈቃድ ከተሰጣቸው ኩባንያዎችም መካከልም ኬሚካል ኢንዱስትሪያል ኃ/የተ/ የግል/ማህበር አንዱ ሲሆን በኢትዮጵያ የተመዘገበና በቻይናዊያን ባለሀብቶች የተመሰረተ በብሮሚን ምርት ላይ ለመሰማራት ያመለከተ ኩባንያ መሆኑ ተጠቁሟል።

ኩባንያው ለስራ ማሰኬጃ 39 ሚሊየን 97 ሺህ 637 የአሜሪካ ዶላር መመደቡ የተገለጸ ሲሆን ከ100 በላይ ቋሚ የስራ ዕድል እንደሚፈጥር ተጠቁሟል።

ሌላኛው ደረራፊቅ ሁስኒ ፋሪስአልቀብ የተባለ ኩባንያም በዮርዳኖስ የተመዘገበና በውጪ ባለሀብቶች የተመሰረተ በግራናይት ምርት ላይ ለመሰማራት ያመለከተ ኩባንያ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን ለስራ መስኬጃ 1 ሚሊየን 16 ሺህ 443 የአሜሪካ ዶላር በጀት መመደቡ ታውቋል፡፡

በተጨማሪም÷ በኢትዮጵያ የተመዘገበውና በኢትዮጵያውያን የተመሰረተው ሰኮያ ማይኒንግ እና ፕሮሰሲንግ ኃ/የተ/ የግል/ማህበር በድንጋይ ከሰል ምርት ላይ ለመሰማራት ያመለከተ ኩባንያ ሲሆን 617 ሚሊየን 912 ሺህ 271 ብር መነሻ ኢንቨስትመንት መመደቡ ተገልጿል።

እንዲሁም በኢትዮጵያ የተመዘገበና በኢትዮጵያዊያን ባለሃብቶች የተመሰረተው አራተኛው ኦሮሚያ ማይኒግ አ/ማህበር ኩባንያ በደለል ወርቅ ምርት ላይ ለመሰማራት ያመለከተ ሲሆን 222 ሚሊየን 875 ሺህ 487 ብር መነሻ ኢንቨስትመንት ካፒታል የመደበ መሆኑን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.