Fana: At a Speed of Life!

ግድቡ የኔ ነው’ የሚለው አባባል በኢትዮጵያውያን ላይ ትልቅ የባለቤትነት ስሜት ፈጥሯል – አምባሳደር ስለሺ በቀለ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ‘ግድቡ የኔ ነው’ የሚለው አባባል ኢትዮጵያውያን በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ላይ ትልቅ የባለቤትነትና የተነሳሽነት ስሜትን እንዲፈጠርባቸው አድርጓል ሲሉ በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደርና የግድቡ ዋና ተደራዳሪ አምባሳደር ስለሺ በቀለ (ዶ/ር ኢ/ር) ገለጹ።

በሕብረት በመሆን ከባድ ፈተናዎችን ጭምር በማለፍ የግድቡን ግንባታ የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ያደረሱ አካላት በሙሉ ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል።

በ2003 ዓ.ም የጀመረው የግድቡ ግንባታ የውሃ አጠቃቀም ትብብርን፣ ፍትሃዊ ተጠቃሚነትና መልካም ጉርብትናን ማዕከል ያደረገ መሆኑን ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ ስትገልጽ ቆይታለች።

ግድቡን በተመለከተ ከግብጽና ሱዳን ጋር የሚደረገው የሶስትዮሽ ድርድርም የጋራ ተጠቃሚነትና ፍትሐዊነትን መሰረት ባደረገ መልኩ መካሄድ እንዳለበትም እንዲሁ።

በፈረንጆቹ ጥር ወር 2020 በአዲስ አበባ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌትና አጠቃላይ ስራን የተመለከተ የሶስትዮሽ ድርድር ተካሄዶ ያለ ስምምነት መጠናቀቁ ይታወሳል።

ይህንን ተከትሎ በወቅቱ የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር የነበሩት አምባሳደር ስለሺ በቀለ ጋዜጣዊ መግለጫ በመስጠት ላይ ሳሉ የተፈጠረውን መቼም እንደማይረሱት መጥቀሳቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በጋዜጣዊ መግለጫው ወቅት ከመካከለኛው ምስራቅ የመጣች ጋዜጠኛ “ግድቡ ሲጠናቀቅ ማን ያስተዳድረዋል?” የሚል ተገቢነት የሌለው ጥያቄ ስታነሳ በሰጡት ምላሽ፤ It’s My Dam ወይም “ግድቡ የኔ ነው” በማለት እኛ ኢትዮጵያውያን እናስተዳድረዋለን የሚል ምላሽ መስጠታቸውን አስታውሰዋል።

ከጋዜጣዊ መግለጫው በኋላ ግድቡ የኔ ነው ወይም #Its My Dam የሚለው አባባል በሁሉም ኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ ቀርቶ ህዝቡ በግድቡ ላይ ያለው የባለቤትነት ስሜት ይበልጥ ከፍ ማለቱን ተናግረዋል።

አባባሉ በኢትዮጵያውያን ላይ ትልቅ የተነሳሽነትና የባለቤትነት ስሜት መፍጠሩንና ለግድቡ ለሚደረገው ድጋፍ ሕዝብን ለማስተባበር ቁልፍ ሚና መጫወቱን ተናግረዋል።

“ለኢትዮጵያውያን የመተባበሪያ፣ የግንኙነትና የጋራ ልማት መልስ እንዲሆን ሊታወስ የሚችል ስንኝ ሆኗል” ሲሉም ገልጸዋል።

በመስሪያ ቤቶች፣ በመኪናዎች ላይ በመገናኛ ብዙሃንና በማህበራዊ ትስስር ገጾች ላይ በስፋት መሰራጨቱንና ይህም በሕዝቡ ላይ የተነሳሽነት ስሜት እንዲኖር ማድረጉን አመልክተዋል።

ግድቡ የኔ ነው ከሚለው አባባል ባሻገር እንደጀመርነው እንጨርሰዋለን፣ ሕዳሴ ግድብ ዳግማዊ አድዋ ነው የሚሉት አባባሎች በኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ የቀሩና ትልቅ አበርክቶ ያላቸው አገላለጾች እንደሆኑ ተናግረዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.