Fana: At a Speed of Life!

የአማራ ክልል ሰላም በተሻለ ደረጃ ላይ ይገኛል – ቢሮው

 

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአማራ ክልል ሰላም በተሻለ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የክልሉ ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ገለጸ።

በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የአሥተዳደር ጉዳዮች አስተባባሪ እና የሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኀላፊ ደሳለኝ ጣሰው በወቅታዊ የክልሉ የሰላም ጉዳዮች ላይ በሰጡት መግለጫ፤ ላለፉት ሰባት ወራት ችግር ገጥሞት የነበረው የአማራ ክልል የሰላም ሁኔታ እየተሻሻለ መሆኑን ተናግረዋል።

ገጥሞ የነበረውን ችግር የአማራ ክልል መንግሥት ለመፍታት ከመከላከያ እና ከክልሉ የጸጥታ ኀይል ጋር በመተባበር በመሥራት የሰላም ሁኔታው እየተለወጠና በማኅበረሰቡ ላይ የሚደርሰው ግፍ መቀነስ መቻሉን ጠቅሰዋል።

እየተደረገ ባለው ውይይት ሕዝቡ ሰላም ፈላጊ መሆኑን እየተናገረ ነው፤ በየመንገዱ የሚፈጸመው ዘረፋ እና እገታ እንዲቆም እየጠየቀ ነው፤ የሰብል ምርት ገበያ እንዲያገኝ፤ የፋብሪካ ውጤቶችም እንዲቀርቡለት እያሳሰበ ነው ብለዋል።

ሕዝቡ ለመከላከያ ሠራዊታችንም አክብሮቱን እያሳየ ሕግ እንዲያስከብር እየጠየቀ ነው፤ በዚህም አንጻራዊ ሰላም እየመጣ ነው ማለታቸውን አሚኮ ዘግቧል፡፡

አቶ ደሳለኝ ከሰላም ማስከበሩ ጎን ለጎንም የጥፋት ኃይል የነበሩትን በሰላማዊ መንገድ እንዲገቡ የሰላም ጥሪ መደረጉን ገልጸው፤ በዚህም ከ12 ሺህ በላይ ወንድሞቻችን ወደ ሕዝብ ተቀላቅለው ማኅበረሰቡን እየካሱ ነው ብለዋል።

በጸጥታ መዋቅሩ ቁጥጥር ሥር የዋሉት ደግሞ ሥልጠና ተሰጥቷቸው ወደ ሕዝብ መቀላቀላቸውን እና መንግሥት ሕግ የማስከበሩን ስራ በትኩረት በመሥራቱ በተገኘው ሰላምም ወደ ልማት መመለስ መቻሉን ጠቅሰዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.