Fana: At a Speed of Life!

በኦሮሚያ ክልል በለውጡ የተገኙ ውጤቶች ለማስቀጠል ያለመ ሰላማዊ ሰልፍ በመጪው ማክሰኞ ይካሄዳል

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል ”ለሰላማችን ዘብ እንቆማለን ለውጡን እናጸናለን” በሚል መሪ ሀሳብ መጋቢት 24 ቀን 2016 ዓ.ም ሰላማዊ ሰልፍ እንደሚደረግ የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ሃላፊ አቶ ሀይሉ አዱኛ እንደገለጹት በክልሉ ሁሉም ዞኖች ከለውጡ በኋላ የተገኙ ውጤቶች ለማስቀጠል ያለመ ሰላማዊ ሰልፍ የፊታችን መጋቢት 24 ቀን ይደረጋል።

በኦሮሚያ ክልል ከለውጡ በኋላ በፖለቲካ፣ በማህበራዊና በኢኮኖሚ መስኮች ከፍተኛ ለውጥ የታየባቸው ውጤቶች መመዝገባቸውን ገልጸዋል።

በፖለቲካ ረገድ ከለውጡ በኃላ በክልሉ የትኛውም የፖለቲካ ድርጅት በሰላማዊ መንገድ መታገል የሚችልበት ምቹ ሁኔታ መፈጠሩንም አንስተዋል።

በኢኮኖሚ ረገድም በግብርና፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በቱሪዝምና በማዕድን ልማት የክልሉን ህዝብ ተጠቃሚ ያደረጉ በርካታ ውጤቶች መገኘታቸውን ጠቅሰዋል።

በተለይም በግብርና ልማት የክልሉ መንግስት የተለያዩ የግብርና ልማት ኢኒሼቲቮችን ቀርጾ ወደ ተግባር መግባቱን ጠቅሰው በዚህም ከፍተኛ እምርታ መታየቱን ገልጸዋል።

በክልሉ በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት፣ በሩዝ እንዲሁም በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት የተገኙ ውጤቶች መልካም ተሞክሮ የተገኘባቸው መሆኑንም አውስተዋል።

በማህበራዊ ልማት ዘርፍም በትምህርት፣ በጤናና ሌሎች የህዝቡን ችግር የሚፈቱ በርካታ የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎች እንደተከናወኑ መጠቆማቸውንም ኢዜአ ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.