Fana: At a Speed of Life!

112 የኮሪደር ልማት ተነሺዎች የጋራ መኖሪያ ቤት እጣ አወጡ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን በኮሪደር ልማት ተነሺ ለሆኑ 112 የአራዳ ክ/ከተማ ወረዳ 8 ነዋሪዎች ዛሬ የጋራ መኖሪያ ቤት እጣ የማውጣት መርሐ ግብር አከናውኗል፡፡

የኮርፖሬሽኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ቶማስ ደበሌ(ኢ/ር) ፥ ቤት ለሰው ልጅ ሁሉ ነገሩ ነው ፤ ለከተማው እድገት ስትሉ በሙሉ ፍቃደኝነት በልማት ከእኛ ጋር ለመጓዝ የፈቀዳችሁ ሁሉ አመሰግናለሁ ብለዋል።

ሁሉም ጥያቄዎች በየደረጃው መልስ አላቸው ፤ ለዚህም የከተማ አስተዳደሩ ለሚነሱ ጥያቄዎች በአግባቡ ለመመለስ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡

በቀጣይ ቀናት ጥያቄያቸውን በመያዝ ከክፍለ ከተማ እንዲሁም ወደ ተቋሙ በመምጣት ተገቢውን መልስ ማግኘት እንደሚችሉም አንስተዋል፡፡

አቅመ ደካማ እናቶች፣አባቶች እና በህመም ምክንያት ወደ ተቋሙ መምጣት የማይችሉትን ከየክፍለ ከተማው በሚቀርቡ መረጃዎች መነሻ በማድረግ የውል አገልግሎት ቤት ለቤት ለመስጠት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

የልማት ተነሺዎቹ አራብሳ ፣ የካ ጣፎ ፣ ጎሮ ስላሴ ፣ ቦሌ ቡልቡላ እና ፋኑኤል ሳይት ያሉ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ላይ እጣ እንዳወጡ ተገልጿል፡፡

ነዋሪዎቹ እጣቸውን በመያዝ እና በደረሳቸው ሳይት በመሄድ ቁልፍ መረከብ ይችላሉ መባሉንም የከተማው ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.