በአደገኛ ዕፅ ዝውውር ወንጀል ጥፋተኛ የተባለው ግለሰብ በ12 ዓመት ጽኑ እስራት ተቀጣ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአደገኛ ዕፅ ዝውውር ወንጀል ጥፋተኛ የተባለው ግለሰብ በ12 ዓመት ጽኑ እስራትና በገንዘብ ተቀጣ፡፡
ታምሩ ፍቅሩ የተባለው ተከሳሽ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ሕግ አንቀጽ 525/1/ለ/ ሥር የተደነገገውን በመተላለፍ ነው አደገኛ ዕጾችን በማዘዋወር ወንጀል በፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የድንበር ተሻጋሪ ወንጀል ችሎት ቅጣት የተላለፈበት።
የፍትሕ ሚኒስቴር ድንበር ተሻጋሪ ወንጀል ዓቃቤ ህግ የክስ መዝገብ እንደሚያስረዳው÷ ተከሳሹ ሐምሌ 23 ቀን 2015 ዓ.ም ከጠዋቱ 1፡30 ከሻሻመኔ ወደ አዲስ አበባ ሊገባ ሲል በሸገር ከተማ ዓለምገና በሚገኘው የመኖሪያ ቤቱ ቅጥር ግቢ ውስጥ 12 ማዳበሪያ (280 ሺህ 501 ግራም) የሚመዝን ካናቢስ በተሸከርካሪ ውስጥ ይዞ ተገኝቷል፡፡
ጉዳዩ በፍርድ ቤት ተጣርቶም ግለሰቡ እንዳይመረት፣ እንዳይዘዋወርና በጥቅም ላይ እንዳይውል በሕግ የተከለከለውን ክልከላ በመተላለፋ በአደገኛ ዕፅ ማዘዋወር ወንጀል ጥፋተኛ ተብሏል።
በዚህ መሰረትም ፍርድ ቤቱ በሕግ የተከለከሉ ዕጾችን የማዘዋወር ወንጀል የፈፀመውን ተከሳሽ በ12 ዓመት ጽኑ እስራት እና በ40 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጣ መወሰኑን የፌዴራል ፖሊስ መረጃ አመላክቷል፡፡