Fana: At a Speed of Life!

ለፈተናዎች ሳንንበረከክ የጀመርነውን ጉዞ ዳር ለማድረስ በትጋት ማገልገላችንን እንቀጥላለን – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ለፈተናዎች ሳንንበረከክ ከችግሮች ባሻገር የበለጸገችውን ኢትዮጵያ ለመገንባት ተደምረን የጀመርነውን ጉዞ ዳር ለማድረስ በትጋት ማገልገላችንን እንቀጥላለን ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡

ከንቲባዋ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው÷ የለውጡ ፍሬያማ ጉዞ ለተጀመረበት 6ኛ ዓመት እና የኢትዮጵያዊነት መሰረት ለሆነው ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ መሰረት ለተጣለበት 13ኛ ዓመት እንኳን አደረሣችሁ ብለዋል፡፡

በለውጡ መሃንዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተመራው የለውጥ ኃይል በብዙ ውስጣዊ እና ውጫዊ ፈተና ውስጥ ሆኖ በርካታ ስኬቶችን በመጎናጸፍ ላይ ይገኛል ሲሉም ገልጸዋል።

ከለውጡ ስኬቶች መካከል የህዳሴ ግድብ ማጠናቀቂያ ምዕራፍ ላይ መድረስ፣ ኢትዮጵያ አረንጓዴ ለብሳ ከስንዴ አስመጭነት ወደ ላኪነት የተሸጋገረችበት፣ የዓድዋ ድል መታሰቢያ ግንባታ ተጠናቆ የተመረቀበት እንደሚገኙበት ገልጸዋል፡፡

እንዲሁም የለውጡ ዓመታት አዲስ አበባ ትኩረት አግኝታ በርካታ ትላልቅ ፕሮጀክቶች ተገንብተው ዓለም አቀፍ የስበት ማዕከል መሆን የጀመረችበት እና በሰው ተኮር ስራዎችም ማኅበራዊ ፍትህ ያነገስንበት ነው ብለዋል፡፡

ቃል በተግባር ተመንዝሮ ኢትዮጵያችን በሕብረ ብሔራዊ ወንድማማችነት የደመቀች ዕድገትዋ መፋጠን የጀመረችበት፣ በመፍጠንና መፍጠር ዕዳዋ እየቀነሰ ምንዳዋ እየጨመረ የመጣች ሀገር እየሆነች ነው ሲሉ አንስተዋል፡፡

ለፈተናዎች ሳንንበረከክ ከችግሮች ባሻገር የበለጸገችዋ ኢትዮጵያን ለመገንባት ተደምረን የጀመርነውን ጉዞ ዳር ለማድረስ በትጋት ማገልገላችንን እንቀጥላለን!

“ምድራዊ ሃይል ሊያስቆመው የማይችለውን የብልጽግና ጉዞ ገብቷችሁ ድጋፋችሁንና ደስታችሁን ለገለፃችሁ ምስጋናዬን ላቀርብላችሁ እወዳለሁ” ብለዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.