Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮ-ሳዑዲ ዓረቢያ ቢዝነስ ፎረም ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 30፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያና ሳዑዲ ዓረቢያ ኩባንያዎች የቢዝነስ ፎረም በዛሬው ዕለት በአዲስ አበባ ተካሂዷል፡፡

በቢዝነስ ፎረሙ የኢትዮጵያ እና ከሳዑዲ ዓረቢያ የመጡ ከፍተኛ የመንግስት አመራሮች እንዲሁም ከ150 በላይ ባለሃብቶች ተሳትፈዋል።

መድረኩ የሀገራቱን የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን መሳብና የቢዝነስ ለቢዝነስ ትስስርን የማጠናከር አላማ ያለው መሆኑ ተመላክቷል።

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የኢኮኖሚ ዳያስፖራ ጉዳዮች ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አክሊሉ ሃይለሚካኤል፥ በፎረሙ ላይ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ኢትዮጵያና ሳዑዲ የረጅም ጊዜ ታሪካዊ እና የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ያላቸው መሆኑን አንስተዋል።

ግንኙነታቸውን ይበልጥ ለማጠናከር መሰል የቢዝነስ ፎረም መድረኮች አስፈላጊ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ ከሌሎች ሀገራት ለኢንቨስትመንት፣ ለንግድና ለቱሪዝም ተመራጭ በሚያደርጓትን ነጥቦች ዙሪያም ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ኢትዮጵያ ለውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ልዩ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፥ በኢትዮጵያ ወደ 229 የሚጠጉ ፈቃድ ያላቸው የሳዑዲ ዓረቢያ ባለሃብቶች መኖራቸውን ገልጸዋል።

በንግዱ ዘርፍ ጥሩ የሚባል እንቅስቃሴ ያለ ቢሆንም የንግድ ሚዛኑ ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ ያመዘነ በመሆኑ ሰፊ ስራ እንደሚጠበቅም ዶክተር አክሊሉ አንስተዋል።

የሳዑዲ ባለሀብቶች በበኩላቸው ቅድሚያ በተሰጣቸው የትኩረት መስኮች ማለትም በግብርና፣ በግብርና ማቀነባበሪያ፣ ሀይል፣ ቱሪዝምና ማዕድን ፍለጋ እንዲሁም ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዘርፎች እንዲሳተፉ ጥሪ መቅረቡን በማድነቅ ሀገራቸው አስፈላጊውን እገዛ እንደምታደርግ ገልጸዋል።

የሳዑዲ ዓረቢያ የውጭ ጉዳይ ምክትል ሚኒስትር አህመድ አል ቃጣን፥ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የረጅም ጊዜ ታሪካዊ ፣ ባህላዊና ማህበራዊ ግንኙነት አጠናክሮ ለመቀጠል ሳዑዲ ዓረቢያ ከምንጊዜውም በተሻለ ዝግጁ መሆኗን ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በሀገሪቱ እያካሄዱ ያሉት ማሻሻያ ኢንቨስተሮች በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ የሚጋብዝ በመሆኑ የሳዑዲ ባለሀብቶችም እድሉን እንደሚጠቀሙ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ፕሬዚዳንት ኢንጂነር መላኩ እዘዘው በበኩላቸው ፥ኢትዮጵያ ኢኮኖሚዋ በማደግ ላይ ያለች ሀገርና ከሳዑዲ ዓረቢያ ጋር ካላት መልካምድራዊ ቅርብት አንጻር ሀገራቱ ብዙ ሊሰሩ እንደሚችሉ ገልጸዋል።

የሳዑዲ ዓረቢያ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ላይ በመሳተፍ የሳውዲ ኢንቨስተሮችን መሳብ እንዲችሉም ጥሪ ማቅረባቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላከትል።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ዳይሬክትር የሆኑት አቶ አስቻለው ታደሰ በበኩላቸው፥ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት አማራጮችና ማበረታቻዎች ዙሪያ ገለጻ አድርገዋል።

በተያያዘ ዜና የኢትዮጵያና የሳዑዲ ዓረቢያ የሁለትዮሽ ውይይት የተለያዩ የመንግስት አካላትንና ተቋማትን ባሳተፈ መልኩ ተካሂዷል።

ውይይቱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደኤታ ወይዘሮ ሂሩት ዘመነ እና የሳዑዲ ዓረቢያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አህመድ አብዱልአዚዝ ቃጣን ውይይቱን በጋራ መርተውታል።

በውይይቱ ከተለያዩ መንግስት መስሪያ ቤቶች የተውጣጡ ሚኒስትር ዴኤታዎች ተሳትፈዋል።

በተካሄደው ውይይት በኢትዮጵያና በሳዑዲ ዓረቢያ መካከል በማዕድን፣በትራንስፖርት፤በባህልና ቱሪዝም፣ በንግድና ኢንቨስትመንት እንዲሁም በሰራተኛና በማህበራዊ መስኮች ያለውን ሁለንተናዊ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል።

ወይዘሮ ሂሩት ዘመነ ኢትዮጵያና ሳዑዲ ዓረቢያ ያላቸውን የረጅም ጊዜ ግንኙነት ውጤታማ ወደ ሆነ የንግድ፣ ኢንቨስትመንትና ቱሪዝም ትስስር ማሳደግ እንደሚገባቸው በመድረኩ ላይ አሳስበዋል።

ሳዑዲ ዓረቢያ በቀጠናው ሰላምና ደህንነት መረጋገጥ የምታደርገውን አወንታዊ ድጋፍም አድንቀዋል።

አህመድ አብዱልአዚዝ ቃጣን በበኩላቸው የሁለቱን ሀገራት ግንኙነቱ ይበልጥ ለማጠናከር በሃገራት መካከል የኢንቨስትመንት ጥበቃና ዋስትና ስምምነት መፈራረም እንደሚያስፈልግ አንስተዋል።

በተጨማሪም ንግድን ለማሳለጥ የሚረዱ ስምምነቶችንና አሰራሮችን ማስቀመጥ እንደሚያስፈልግና ሳዑዲአረቢያም ኢትዮጵያ ዓለም አቀፉን የንግድ ድርጅት እንድትቀላቀል ድጋፏን እንደምትሰጥ አረጋግጠዋል።

በኢትዮጵያ ለሶስት ቀናት የስራ ጉብኝት እያደረገ የሚገኘው የሳዑዲ ዓረቢያ የልዑካን ቡድን ዛሬ ምሽት የስራ ጉብኝቱን አጠናቆ የሚመለስ ይሆናል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.