የአሜሪካ የትራንስፖርት ደኅንነት አስተዳደር በአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ያደረገው የአቪዬሽን ሴኪዩሪቲ ኦዲት በስኬት ተጠናቀቀ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 28፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአሜሪካ የትራንስፖርት ደኅንነት አስተዳደር በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ያደረገው የአቪዬሽን ሴኪዩሪቲ ኦዲት በስኬት መጠናቀቁን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት አስታወቀ፡፡
አገልግሎቱ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው÷ የአሜሪካ የትራንስፖርት ደኅንነት አስተዳደር (ቲ ኤስ ኤ) ከመጋቢት 23 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ለአምስት ተከታታይ ቀናት በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የአቪዬሽን ሴኪዩሪቲ ኦዲት ሲያከናውን ቆይቷል፡፡
ልዑኩ በቆይታው÷ የመንገደኞች፣ የሻንጣ፣ የካርጎ ጭነቶች፣ የዙሪያ ጥበቃና ፍተሻ እንዲሁም የአውሮፕላን ደኅንነትን ለማረጋገጥ የሚወሰደው የሴኪዩሪቲ እርምጃ ከዓለም አቀፍ አሰራር አንጻር አጠቃላይ ያለበትን ደረጃ በተመለከተ ሁሉን አቀፍ ኦዲት አድርጓል፡፡
በኦዲቱ ጥልቅ የሠነድ ግምገማ እና የአካል ምልከታ መደረጉም ተገልጿል፡፡
በልዑኩ በቀረበው የማጠቃለያ ሪፖርት እንደተገለጸውም ወደ አሜሪካ ሀገር በሚደረጉ በረራዎችም ሆነ አጠቃላይ በአቪዬሽን ሴኪዩሪቲ ኦፕሬሽናል ሂደቶች ላይ ምንም ዓይነት የደኅንነት ስጋት እንደሌለ በድጋሚ ተረጋግጧል፡፡
በኢትዮጵያ ጠንካራ የሆነ የአቪዬሽን ሴኪዩሪቲ ስርዓት መገንባቱን እንዲሁም በቀጣይም በአፍሪካ ምርጥ የአቪዬሽን ሴኪዩሪቲ አገልግሎት ሰጪ ተቋም ለመሆን የተያዘውን ስትራቴጂክ ዕቅድ ለማሳካት የሚያስችል መሰረት እንደተጣለም የትራንስፖርት ደኅንነት አስተዳደር ተወካይ ገልጸዋል፡፡
በሁለቱ ተቋማት ብሎም ሀገራት መካከል በዘርፉ የሚደረገው ትብብር ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ነው ያረጋገጡት፡፡
በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የሲቪል አቪዬሽን ደኅንነት ዋና መምሪያ ዳይሬክተር አስራት ቀጀላ በበኩላቸው÷ በአገልግሎቱ በተሰጠው ልዩ ትኩረት በሲቪል አቪዬሽን ደኅንነት ዋና መምሪያ የተደረገው ሁሉን አቀፍ ሪፎርም፣ የተዘረጋው አሰራር፣ የሰው ኃይል ልማት፣ የቴክኖሎጂ እምርታ እና የአውሮፕላን ማረፊያ ባለድርሻ አካላት ቅንጅት የትራንስፖርት ደኅንነት አስተዳደርን እና ከዚህ ቀደም የተደረጉ ሌሎች ተከታታይ ዓለም አቀፍ የአቪዬሽን ሴኪዩሪቲ ምዘናዎችን ስኬት ለመጎናፀፍ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማበርከታቸውን አስረድተዋል፡፡
በኦዲቱም ለተገኘው ሀገራዊ ውጤት ሌት ተቀን ሲተጉ ለነበሩ የዋና መምሪያው ሠራተኞችና አመራሮች እንዲሁም በአውሮፕላን ማረፊያው ለሚገኙ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በቀጣይ በሚደረገው ሀገራዊ የዓለም አቀፍ ሲቪል አቪዬሽን ድርጅት (አይ ሲ ኤ ኦ) ኦዲትም ሁሉም በከፍተኛ ቅንጅት፣ ቁርጠኝነት እና ትብብር በመስራት ኢትዮጵያን በከፍታ ማስጠራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
ለሀገራዊ ኦዲቱም ከወዲሁ ስራዎች ተለይተው እየተከናወኑ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡
የአሜሪካ የትራንስፖርት ደኅንነት አስተዳደር ከሐምሌ 10 እስከ ሐምሌ 12 ቀን 2015 ዓም ድረስ በቦሌ ዓለም አቀፍ የአውሮፕላን ማረፊያ ባካሄደው የበረራ ደኅንነት ልዩ ኦዲት በዓለም አቀፍ አሰራር መሰረት ምንም አይነት የደኅንነት ክፍተት (ግኝት) እንደሌለበት መግለጹ ይታወሳል፡፡
የአሜሪካ የትራንስፖርት ደኅንነት አስተዳደር ኃላፊ ዴቪድ ፕኮስኬ የኦዲት ውጤት መገኘቱን ተከትሎ ነሐሴ 28 ቀን 2015 ዓ.ም ወደ ኢትዮጵያ መጥተው በተቋሙ ባደረጉት ጉብኝት÷ ለኢትዮጵያ የበረራ ደኅንነት አጠባበቅ አድናቆታቸውን መግለጻቸውም ይታወቃል፡፡
በመጨረሻም በዋና መምሪያው የተጀመረውን ሪፎርም አጠናክሮ በማስቀጠልና በአውሮፕላን ማረፊያው የሚገኙ ሁሉንም በላድርሻ አካላት አቀናጅቶ በማነቃነቅ ለህብረተሰቡ ተገቢውን አገልግሎት ለመስጠት አሰራሮች ተዘርግተው እየተተገበሩ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡
ተገልጋዩ በአውሮፕላን ማረፊያው ማህበረሰብ ከሚሰጡ አገልግሎቶቾ ጋር በተያያዘ አስተያየትና ቅሬታ ሲኖረው በአውሮፕላን ማረፊያው ውስጥ በተዘረጋው የአስተያየትና የጥቆማ መስጫ ስርዓት በግልጽ ሀሳቡን በመስጠት የተሻለ አገልግሎት ማግኘት እንዲችል በቅንጅት እየተሰራ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡