ጠ/ሚ ዐቢይ (ዶ/ር) ኢትዮጵያና ሩዋንዳ በግብርናው ዘርፍ የሚያደርጉት ትብብር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገለጹ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 28፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ እና ሩዋንዳ በግብርናው ዘርፍ የሚያደርጉትን ትብብር አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስታወቁ፡፡
ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት ዛሬ ወደ ሩዋንዳ ኪጋሊ ያቀኑት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)÷ በፕሬዚዳት ፖልካጋሜ ለተደረገላቸው አቀባበል አመስግነዋል፡፡
በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍም÷ በሩዋንዳ ያለውን እድገት በመመልከታቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል፡፡
የሩዋንዳ መንግሥትም የሀገሪቱን እድገት ለማስቀጠል የሚያደርገውን ጥረት አድንቀዋል፡፡
ኢትዮጵያ እና ሩዋንዳም ለግብርና ልማት ስኬት በፅናት እየሠሩ መሆናቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡
ይህ በጎ ተፅዕኖም ወደቀጣናው እንዲስፋፋ በጋራ ለመሥራት ዝግጁ መሆናቸውን ነው ያረጋገጡት፡፡