ስታርት አፖችን ወደ ገበያ ለማስገባት እየተሠራ ነው ተባለ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 4፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ ስታርት አፖችን በፍጥነት፣ በጥራትና በስፋት ወደ ገበያ ለማስገባት ሥነ-ምኅዳሩን ምቹ የማድረግ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
እስከ ሚያዝያ 20 ቀን 2016 ዓ.ም የሚቆይ የኢትዮጵያ “ስታርት አፕ” ዐውደ -ርዕይ በሣይንስ ሙዝየም ለጎብኚዎች ክፍት ተደርጓል።
ስታርት አፖች ያሉ መልካም ዕድሎችን ተጠቅመው ውጤታማ እንዲሆኑ የመደገፍ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴዔታ ባይሳ በዳዳ (ዶ/ር) ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡
ለዚህም የአጭር፣ የመካከለኛና የረጅም ጊዜ የድጋፍ ማዕቀፎች ተግባራዊ እየተደረጉ መሆኑን ጠቁመው÷ በኢትዮጵያ ስታርት አፖችን ለመደገፍና ለማበረታታት የተዘረጋው አሠራር የውጭ ስታርት አፖችን እንደሚጋብዝ ጠቅሰዋል፡፡
ለአብነትም የመሥሪያ ቦታ፣ የቴክኒክና የፋይናንስ ድጋፍ የሚያገኙበት ሁኔታ እንደሚመቻች ገልጸዋል፡፡
ለተመልካች ክፍት በሆነው ዐውደ-ርዕይ ላይም÷ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ ግብርና፣ ጤና፣ ትምህርት፣ ኢንዱስትሪ፣ በፋይናንስና ሌሎች ዘርፎች የተሰማሩ ጀማሪ ሥራ ፈጣሪዎች መሳተፋቸውን አብራርተዋል፡፡
የዐውደ-ርዕዩ ዓላማም ስታርት አፖች ያላቸውን ምርት፣ አገልግሎትና ፈጠራ÷ ተቋማት፣ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና ተማሪዎች እንዲጎበኙት ከማስቻል ባለፈ በባለሃብቶችና ስታርት አፖች መካከል ትስስር እንዲፈጠር ማድረግ መሆኑን አመላክተዋል፡፡