Fana: At a Speed of Life!

በአማራ ክልል 169 ሚሊየን ኩንታል ምርት ለማምረት ታቅዶ እየተሰራ ነው

 

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 4፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል በ2016/17 የመኸር ምርት ዘመን 169 ሚሊየን ኩንታል ምርት ለማምረት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

የክልሉን ምስራቃዊ አካባቢዎችን መሠረት ያደረገ የምርት ዘመኑ የሰብል ልማት ንቅናቄ መድረክ “ግብርና ከማምረትም በላይ ነው” በሚል መሪ ሀሳብ በደሴ ከተማ የክልል፣ የዞንና የወረዳ አመራሮችና ባለሙያዎች በተገኙበት ተካሂዷል።

በምርት ዘመኑ በተለየ መልኩ ለመስራት ታቅዷል ያሉት የክልሉ ግብርና ቢሮ ሀላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ/ር)፤ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የህዝቡን ችግር ለመፍታት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

በክልሉ 5 ነጥብ 2 ሚሊየን ሄክታር መሬትን በመኸር ሰብል በማልማት 169 ሚሊየን ኩንታል ምርት ለማምረት እየተሰራ መሆኑም ተመላክቷል፡፡

ለዚህም 8 ነጥብ 5 ሚሊየን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ግዥ እየተፈፀመ መሆኑ የተገለፀ ሲሆን፤ 300 ሺህ ኩንታል ምርጥ ዘር መዘጋጀቱም ተጠቁሟል።

ባለፈው የምርት ዘመን በነበረው የፀጥታ ችግርና በአንዳንድ የክልሉ አካባቢዎች በተከሰተው ድርቅ ምክንያት ምርታማነቱ ቀንሶ እንደነበረም አስታውሰዋል።

በ2016/17 የምርት ዘመን ያለፈውን ሊያካክስ በሚችል መልኩ ነው ለመስራት የታቀደው ያሉት ሀላፊው በሁሉም አካባቢዎች የማዳበሪያ ስርጭቱ እየተከናወነ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

አርሶአደሩ ሙሉ በሙሉ ትኩረቱን በግብርናው ስራ ላይ ማድረግ እንዳለበትም ነው ድረስ ሳህሉ(ዶ/ር) ያስገነዘቡት።

በይከበር አለሙ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.