Fana: At a Speed of Life!

ፋና ላምሮት ሀገር አቀፍ የኪነ-ጥበብና የባህል ፌስቲቫል ማቀጣጠያ ሻማ በሚሆንበት አግባብ ላይ በትኩረት ይሰራል – አቶ አድማሱ ዳምጠው

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ፋና ላምሮት ሀገር አቀፍ የኪነ ጥበብ እና የባህል ፌስቲቫል ማቀጣጠያ ሻማ በሚሆንበት አግባብ ላይ በትኩረት ይሰራል ሲሉ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ዋና ሥራ አስፈጸሚ አቶ አድማሱ ዳምጠው ገለጹ፡፡

በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው 4ኛው የአሸናፊዎች አሸናፊ የፋና ላምሮት የፍጻሜ ውድድር በደማቅ ሥነ-ሥርዓት እየተካሄደ ነው፡፡

የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አድማሱ ዳምጠው÷ ፋና ላምሮት በቀጥታ ስርጭት በባለሞያዎች እና በሕዝብ ዳኝነት የድምጽ የባለ ተሰጥኦ ውድድር ታሪክ የራሱን ደማቅ አሻራ በልዩነት አስቀምጧል ብለዋል፡፡

ፋና ላምሮት እድል ላላገኙት እድል እና ተስፋ ከመፈጠሩ ባሻገር አዲስ የሙዚቃ ትውልድ በማስተዋወቅ እና ወደ ኢንዱስትሪው በማስገባት የራስን ልዩ አሻራ በማሳረፍ የሚዘልቅ የቤተሰብ የመዝናኛ ፕሮግራም ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡

ሙዚቃ አምረው በሚሰደሩ ስንኞች በጣዕመ ዜና፣ በአካል እና በመንፈስ የመሰብሰብ ሃይል ባለቤት፣ የማህበራዊ ትስስር ፈትል ድንቅ የፍቅር ቋጠሮ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ክብር ለሚገባው ክብር እየሰጠ ትውልድ ክብሩ እንዲጋባበት መታያ እና መድመቂያ ሜዳ በመፍጠር እና ጥበብ በትውልድ ውስጥ ሀገር ሆኖ ሀገር እንዲገነባ መስራት ቀዳሚ አላማው ነው ብለዋል፡፡

በዚህም ፋና ላምሮት የተሰኘ ማዕድ ዘርግቶ በየሳምንቱ ሙዚቃ እየደገሰና በየምዕራፉ እንቁ ባለሙያዎቸን እያፈራ የሙዚቃ አምሮትን የሚቆርጡ ውድድሮችን ለአድማጭ ተመልካች ማድረሱን ቀጥሎ 4ኛ ምዕራፍ የአሸናፊዎች አሸናፊ ላይ መድረሱን አስገንዝበዋል፡፡

ፋና ላምሮት በአራት ዓመታተ የሥኬት ጉዞው የፋና ምልክት፣የውድድሮች ሁሉ አውራ ሆኖ መዝለቁ የአድማጭ ተመልካቶች ቀና ዳኝነት፣ የሙዚቃ ተጫዋቾች እና ዳኞችን ጨምሮ የመላው የጥበብ ቤተሰብ ተሳትፎ ውጤት መሆኑንም በአክብሮት ገልጸዋል፡፡

ሙዚቃ የሀገር ፍቅርን ከቃል በላይ በተግባር ያሳዩ እና በሥራቸው ከከዋክብት በላይ የሚያበሩ ከእንቁ በላይ የከበሩ ባለሙያዎችን እንዳበረከተም ጠቅሰው÷ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትም ትውልድ እንደ ጅረት ተሰናስሎ ሲፈስ የሙዚቃ ትውልድም ተከታትሎ እንዲቀጥል እንደሚፍልግ ነው ያስገነዘቡት፡፡

ፋና ላምሮት ያለፉት እንዲታወሱ፤ ያሉት እንዲከበሩ እና መጪዎች ቀደምቶቻቸውን እንዲተኩ በማሰብ በትኩረት ተዘጋጅቶ ለአድማጭ ተመልካች እንደሚቀርብም አስረድተዋል፡

ዛሬ በሚከናወነው 4ኛው የአሸናፊዎች አሸናፊ የፋና ላምሮት የፍጻሜ ውድድርም የሙዚቃ መድረክ አዲስ ከዋክብትን ያገኛል ነው ያሉት፡፡

የፋና ላምሮት ውድድር÷ ተሳታፊዎች አንዴ ተወዳድረው ካጠናቀቁ በኋላ የሚበተኑበት ሳይሆን ሙያና ሙያተኛው ቤተሰባዊ ትስስር ፈጥረው ፋና ላምሮትን እንደ ልህቀት ማዕከል እንዲገለገሉበት በቀጣይ ሰፊ ሥራ ለመስራት መታቀዱንም ጠቁመዋል፡፡፡

ፋና ላምሮት ሀገር አቀፍ የኪነ ጥበብ እና የባህል ፌስቲቫል ማቀጣጠያ ሻማ በሚሆንበት አግባብ ላይም አበክረን እንሰራለን ብለዋል፡፡

ለአዳዲሶቹ መድረክ ስንፈጥር የቀደሙት የሀገር እና የትውልድ ባለውለታዎችን ማሰባሰብ እንዲታወሱ ብቻ ሳይሆን በሞያቸው ተከብረው ያለፉበትን ተሞክሮ ለትውልድ እንዲያካፍሉ መድረክ ማመቻቸትን ታሳቢ አድርገናልም ብለዋል፡፡

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በቀጣይ ከመዝናኛ ኢንዱስትሪው ባሻገር መረጃ እና እውቀትን የሚያስጨብጡ አዳዲስ የሚዲያ ይዘቶችን አሰናድቶ ወደ አድማጭ ተመልካች እንደሚያደርስም ተናግረዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.